Fana: At a Speed of Life!

ትራማዶልን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጠቀም ለድንገተኛ ሞት ያጋልጣል ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ትራማዶልን ከሐኪም ፈቃድ ውጪ በአንድ ጊዜ አብዝቶ መውሰድ ከድንገተኛ ሞት እስከ ቀጣይነት ያላቸው የጤና ዕክሎች እንደሚያጋልጥ ተጠቆመ፡፡

ትራማዶል የተሰኘው ጊዜያዊ የህመም ማስታገሻ ተገቢ ባልሆነ መንገድ እየተዘወተረ እና ሱስ እየሆነ የወጣቶችን ጤና እያመሳቀለ መሆኑን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር መስፍን በኃይሉ ገልጸዋል፡፡

በአብዛኛው ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በትራማዶል ሱስ እንደሚጠመዱ ጠቅሰው÷ ያለ በቂ ምክንያት እና ተዘውትሮ ሲወሰድ ወደ ሱስነት እንደሚሸጋገር አስረድተዋል፡፡

የትራማዶል ሱስ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ያለ አደገኛ የሥነ-አዕምሮ ችግር ነው ያሉት ባለሙያው÷ ከድንገተኛ ሞት እስከ ቀጣይነት ያላቸው የጤና እክሎች እንደሚያስከትል አስረድተዋል፡፡

በአንድ ጊዜ በብዛት ከተወሰደም ለሞት ይዳርጋል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም የአንጎል ንዝረት፣ የኩላሊት መድከም (መባባስ)፣ ለጡንቻ መቅለጥ እና ለከፋ የሥነ-ልቦና ችግር እንደሚዳርግ አንስተዋል፡፡

አንዳንድ ወጣቶች ኪኒኑን በመውሰድ ሱሳቸውን ማብረድ ሲሳናቸው በመርፌ መውሰድ እንደሚጀምሩ አመላክተው÷ ይህ ሁኔታም ለስትሮክ እንደሚያጋልጥ ጠቁመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.