Fana: At a Speed of Life!

እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ መቀነስ የሁሉንም አካላት አርበኝነት የሚጠይቅ ነው – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ መቀነስ የሁሉንም አካላት አርበኝነት የሚጠይቅ ነው ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

እኛም በዘመናችን በተሰማራንበት የስራ መስክ አርበኛ እንሁን፤ ዜጎቻችንን ከትራፊክ አደጋ እንጠብቅ በማለት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከል መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የትራፊክ አደጋ በየአመቱ በርካታ ውድ ነፍሶችን እንድናጣ በንብረትና አካል ላይ መራር አደጋ እንዲደርስ እያደረገ ያለ ጠላት ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ የዘንድሮ የዓድዋ ድል በዓል በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሰው ህይወት መጥፋት የለበትም በሚል በተቋሙ እንደሚዘከር ተናግረዋል::

68 በመቶ በአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስና ቸልተኝነት የሚመጣ አደጋ እንዲሁም 14 በመቶ በተሽከርካሪ ቴክኒክ ምክንያት የሚደርሰውን አደጋ መቀነስ የሁሉም አካላት አርበኝነት የሚጠይቅ ነውም ብለዋል።

አሸከርካሪዎች፣ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ፣ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛዎች፣ የተሽከርካሪ መርማሪዎች፣ ሕግ አስከባሪ አካላት በከፍተኛ የአርበኝነት ስሜት ለሀገርና ለህዝብ ቅድሚያ በመስጠት ውድ የሰው ህይወትና የንብረት ውድመትን በማትረፍ 82 በመቶ አደጋን መቀነስ እንደሚቻልም አስገንዝበዋል።

በመሆኑም 128ኛውን የዓድዋ ድልን ስንዘክር የትራፊክ አደጋን በአርበኝነት ቆመን ለመቀነስ ቃላችንን በማደስ መሆን አለበት ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.