በዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ኢትዮጵያ በ14 አትሌቶች ትወከላለች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በስኮትላንድ በሚካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ኢትዮጵያ በሥድስት ወንድ እና በስምንት ሴት አትሌቶች ትወከላለች፡፡
በዚህም መሰረት በሴቶች 800 ሜትር አትሌት ሀብታም ዓለሙ፣ ጽጌ ዱጉማ ሲካፈሉ ወርቅነሽ መሰለ በተጠባባቂነት ተይዛለች።
እንዲሁም በ1 ሺህ 500 ሜትር አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ ድርቤ ወልተጂ እና ብርቄ ኃየሎም ይሳተፋሉ፡፡
ለምለም ኃይሉ፣ ጉዳፍ ፀጋይ እና ሒሩት መሸሻ በ3 ሺህ ሜትር ኢትዮጵያን ሲወክሉ÷ መልክናት ውዱ በተጠባባቂነት ተይዛለች።
በወንዶች 3 ሺህ ሜትር ሰለሞን ባረጋና ጌትነት ዋሌ የተካተቱ ሲሆን÷ ጥላሁን ኃይሌ በተጠባባቂነት ተይዟል።
በሌላ በኩል አትሌት ሳሙኤል ተፈራና ቢኒያም መሐሪ በ1 ሺህ 500 ሜትር ኢትዮጵያን ይወክላሉ።
በ800 ሜትር አትሌት ኤፍሬም መኮንን በብቸኝነት ኢትዮጵያን እንደሚወክል ታውቋል፡፡
በስኮትላንድ ግላስጎው በሚደረገው 19 ዓይነት የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር÷ 20 የዓለም ሻምፒዮኖች፣ 7 የኦሊምፒክ አሸናፊዎች፣ 18 ያለፈው የቤት ውስጥ አሸናፊዎች ይሳተፋሉ፡፡
በአጠቃላይ ከ133 ሀገራት የተውጣጡ 651 አትሌቶች በውድድሩ እንደሚካፈሉ ተገልጿል፡፡
በወርቅነህ ጋሻሁን