ሩሲያ የምሥራቅ ዩክሬኗን አዲቪካ ከተማ ተቆጣጠረች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ወታደራዊ ኃይሎች በምሥራቃዊ ዩክሬን የምትገኘውን የአዲቪካ ከተማን መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከተማዋ በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር የዋለችው የአሜሪካ ወታደራዊ እርዳታ መዘግየቱን ተከትሎ ዩክሩን የተተኳሽ እጥረት ስላጋጠማት አዲቪካን ለቃ መውጣቷን ተከትሎ ነው፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያ ወታደራዊ ኃይሎች ከተማዋን መቆጣጠራቸው ለጦሩ ወሳኝ ድል መሆኑን ገልፀው÷ የእንኳን ደስአላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሩሲያ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የምሥራቃዊ ዩክሬኗን ባክሙት ከተማ ከተቆጣጠረች ወዲህ ይህ ሁለተኛው ትልቁ ድሏ መሆኑን ጠቅሶ ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ሁለት ዓመታትን ሊደፍን በተቃረበው የሁለቱ ሀገራት ጦርነት ዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ዕቅዷ በሩሲያ ኃይሎች መክሸፉ ተገልጿል፡፡
በአንፃሩ የሩሲያ ጦር ኬዬቭን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አጠናክረው መቀጠላቸው ተጠቅሷል፡፡