የማህበራዊ ምህንድስና የሳይበር ጥቃትና መከላከያ መንገዶቹ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ማህበራዊ ምህንድስና ማለት የሰዎችን አመለካከትና የሰው ልጆችን መስተጋብር በመጠቀም ወይም በማታለል ሰርጾ በመግባት ሚስጥራዊ መረጃን በማግኘትና ለራስ ጥቅም በማዋል የሚፈጸም የጥቃት ዓይነት ነው።
የማህበራዊ ምህንድስና ጥቃት የሰው ልጆችን ድክመት ለራስ ጥቅም እንዴት ማዋል እንደሚቻል የማሰብ ጥበብ ላይ ትኩረት በማድረግ በዓለማችን ላይ በስፋት የሚፈጸም የሳይበር ጥቃት ዓይነት ነው፡፡
ለማህበራዊ ምህንድስና ጥቃት ዋነኛ መሳሪያ ሆኖ የሚያገለግለው ደግሞ የሰው ልጆች ንቃተ ህሊና በጉዳዩ ላይ አናሳ መሆንና ቸልተኝነት እንደሆነ ይነሳል፡፡
የማህበራዊ ምህንድስናን በአግባቡ ያለመረዳትና ስለሀሳቡ ዝቅተኛ የሆነ ንቃተ ህሊና መኖር በሳይበሩ ዓለም የሚደርሱ የማህበራዊ ምህድስና ጥቃቶችን ለመከላከል ወይም ለማስቀረት የሚኖረውን እድል ዝቅተኛ እንደሚያደርግም ነው የሚነገረው፡፡
ማሕበራዊ ምህንድስናን ለመከላከል ዋነኛው መፍትሔ፡-
• የማህበራዊ ምህንድስናን ጥቃቶች መከላከልና የሚደርሱ ጉዳቶችንም ማስቀረት የሚቻልበት ዋነኛው መንገድ የሰው ልጆችን ንቃት ሕሊና ከፍ በማድረግና አስተሳሰቦችን መቀየር ነው፤
• ማህበራዊ ምህድስና የራስን ጠቃሚ መረጃ በራስ ስህተት ለተቃራኒ አካል አሳልፎ መስጠትና የጥቃትና ጉዳት ሰለባ መሆንን መገንዘብ፤
• ለዚህም የመረጃ አጠቃቀምን በብልሃትና በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት፣ መረጃዎች ጠቃሚ ሚስጢሮችን በልዩ ሁኔታ ከተደራሽነት መገደብን፤
• ሁሌም የመረጃን ወሳኝነትና የመረጃ አለአግባብ ብክነትን መከላከል፤
• ኢ-ሜይልን ጨምሮ ሌሎች የመረጃ መለዋወጫና መገናኛ ዘዴዎችን እንዲሁም የማሕበራዊ ሚዲያ አማራጮችን ደህነንታቸው በተጠበቀ መንገድ መጠቀም፤
• ስለማህበራዊ ምህንድስና ተገቢውን ዕውቀት በማዳበርና በአንክሮ በማሰብ ራስንና ሌሎችን ከማህበራዊ ምህንድስና ጥቃት መከላከል እንደሚቻል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር መረጃ ያመላክታል፡፡