የአፍሪካ ሀገራት የሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሀገራት አካታችና ዘላቂነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ የሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን አመላከተ።
44ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የአፍሪካ ኅብረት የኢኮኖሚ ልማት፣ ቱሪዝም፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ማዕድን ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር÷ በአፍሪካ አካታችና ዘላቂነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ ሀገራት በሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት መሥራት አለባቸው ብለዋል።
በአፍሪካ በሥራ ገበታ ላይ ካለው የሰው ኃይል መካከል 15 ነጥብ 8 በመቶው በበቂ ደረጃ ተፈላጊውን ክኅሎት ይዘው እየሠሩ አለመሆኑን ጥናቶች ማመላከታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ሥራ ፈላጊው እና በአፍሪካ ያለው የሥራ ገበያ አለመጣጣም አኅጉሩን እየፈተኑ ካሉ ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን ገልጸው÷ ሀገራት መሰል ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ፖሊሲና አሠራር ሊዘረጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ከዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ 2 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ÷ ይህም የአፍሪካ ሀገራት በበቂ መጠን ምርት እያመረቱ አለመሆኑን ያሳያል ብለዋል።
በመሆኑንም የግብርና ምርትን ማሳደግ፣ የተቀነባበሩና እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን በስፋት ማምረትና ለዓለም ገበያ ማቅረብ ላይ በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አምራች ዘርፉ ለአፍሪካ አጠቃላይ ዓመታዊ የምርት ዕድገት የ11 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው÷ በመስኩ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
አካታችና ዘላቂ እድገት ለማምጣት ከኀብረቱና ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በመሆን በአፍሪካ የሰው ኃይል ልማት፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ መፍትሄ ጠቋሚ ጥናት እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡
ጥናቱም በፈረንጆቹ 2024 የሚጠቀናቀቅ ሲሆን÷ የአፍሪካን የዓለም ንግድ ድርሻ ማሳደግና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳካት ከያዛቸው ጥቅል ግቦች መካከል ይገኝበታል ነው ያሉት፡፡
በማብራሪያቸው ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የቴክሎጂ ፈጠራዎችን ማስፋፋት ቁልፍ በመሆናቸው ሀገራት አጽንኦት ሊሰጧቸው እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!