ማዚ ፒሊፕ – ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የአሜሪካ ኒውዮርክ ኮንግረስ አባል እጩ ተወዳዳሪ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ማዚ ፒሊፕ በአሜሪካ ውስጥ ፖለቲከኛ ሲሆኑ፥ በእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ጆርጅ ሣንቶስ ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ራሳቸውን ለማበልጸግ ተጠቅመውበታል፤ ህግ ጥሰዋል የሚል ሪፖርት ከወጣባቸው በኋላ ከስልጣናቸው መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም የኒውዮርክ ሦስተኛው ኮንግረስ ዲስትሪክት ያላለቀ 11 ወራት የስልጣን ዘመናቸውን ማን እንደሚያጠናቅቅ በምርጫ እንደሚወሰን ይጠበቃል፡፡
በዚህም ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ማዚ ፕሊፕ እና የቀድሞ የአሜሪካ የዲሞክራቲክ ተወካይ ቶም ሱዚ ይወዳደራሉ ነው የተባለው፡፡
ማዚ ፒሊፕ በኢትዮጵያ የገጠር ክፍል ተወልደው ያደጉ ሲሆኑ፥ ባደጉበት አካባቢም ውሃን ጨምሮ ኤሌክትሪክና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በአግባቡ እንዳልነበር ይነገራል፡፡
በ12 ዓመታቸው፤ ማለትም በፈረንጆቹ 1991 ወደእስራኤል በመሄድ ኑሯቸውን እንደቀጠሉም ነው የታሪክ ማህደራቸው የሚያነሳው፡፡
18 ዓመት ሲሆናቸውም የእስራኤልን መከላከያ ሠራዊት በመቀላቀል ሲያገለግሉ የቆዩና ከዚያ በኋላም ትምህርታቸውን በሃይፋ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲውም የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ሊቀመንበር እንደነበሩና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በዚሁ ዩኒቨርሲቲ እንዳጠናቀቁ ይነሳል፡፡
በቀጣይም በቴል-አቪቭ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በዲፕሎማሲና ሴኪዩሪቲ ይዘው አጠናቀዋል፡፡
ከዚያም ወደአሜሪካ በመሄድ ኑሯቸውን እዚያ በማድረግ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን መጀመራቸው ይነሳል፡፡
በፈረንጆቹ ጥቅምት 2021 ኢትዮጵያዊቷ ማዚ ፒሊፕ ሪፐብሊካን በመሆን ለኒውዮርክ የናሶ ግዛት ህግ አውጪ በመሆን ለአራት ጊዜ ስልጣን ላይ የነበሩትን ኤለን ቢርንባምን በ7 በመቶ ድምጽ በማሸነፍ መመረጣቸው የታሪክ መዝገባቸው ያሳያል፡፡
ይህን መሰል የፖለቲካ ተሳትፏቸውና አቋማቸው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኙ ማድረጉም ነው የሚነገረው፡፡
ማዚ በኮንግረስ ውስጥ ለህዝብ ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጡ፣ ለኢኮኖሚው መፍትሄ በማበጀት ስራ የሚጠመዱ፣ የድንበር ደህንነት ላይ የማያወላውል አቋም ያላቸው እና ለታክስ እፎይታ መሰጠት አለበት በሚል ሰብዓዊነትን ባስቀደመ ውሳኔያቸው በብዙዎች ልብ ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗቸዋል ተብሏል፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ማዚ ሜሌሳ ፒሊፕ ቀጣይ የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት የኒውዮርክ 3ኛ ኮንግረስ ዲስትሪክት ተወካይ እንደሚሆኑ በብዙዎች ተገምቷል፡፡
ምንጭ፡- ኤፒ ኒውስ እና ዊኪፒዲያ
#Ethiopia #USA #newyork
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!