አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሄራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይታቸውም ÷ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ በዩኤንዲፒ የተለያየ ድጋፍ እንደተደረገለት ተጠቅሷል።
ዩኤንዲፒ በሰዉ ሀይል፣ በአደረጃጀት፣ በፕሮግራም ዝግጅት፣ በቢሮ መገልገያና በተሽከርካሪ ድጋፍ ማድረጉን ኮሚሽነሩ አንስተዋል፤ ድጋፉ የተቋሙ ተልዕኮ ዉጤታማ እስኪሆን ድረስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የዩኤንዲፒ የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ በበኩላቸዉ÷ የተጀመሩ የድጋፍና የትብብር ስራዎች ተጠናክረው እንዲሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በቀጣይም የትብብር ግንኙነቱን ማዕከል የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም የተዘጋጀውን ፕሮግራም ማሳካት ላይ መረባረብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ፕሮግራሙን ለማሳካትም ሀብት ማሰባሰብ ላይ ትኩረት አድርገዉ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡