Fana: At a Speed of Life!

የፓተንት ሕግን ለማሻሻል የሚያስችል ምክክር እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የፓተንት ሕግን ለማሻሻል የሚያስችል ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በላይ በፓተንት ሕጓ ላይ ማሻሻያ ሳታደርግ መቆየቷን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል በውይይቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

የፓተንት ሕጉ አሁን ካለው ዓለም አቀፍ የፓተንት ሕግ ጋር ሲወዳደር ብዙ ክፍተት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ይህን ለማሻሻል ባለስልጣኑ ለሁለት ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው÷ የውይይት መድረኩም ሕጉን ለማሻሻል የሚያግዙ ግብዓቶችን ለመሰብሰብ እንደሚያስችል ታስቦ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

እያደገ ያለው የቴክኖሎጂና የኢንዱስትሪ ዘርፍ በፈጠራ ሥራዎች እንዲታገዝ÷ የፈጠራ ሥራዎችን መጠበቅ የሚያስችልና ከዓለም አቀፉ ሕግ ጋር የተዛመደ ሕግ እንደሚያስፈልገውም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

መድረኩን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን እና የአውሮፓ የፓተንት ቢሮ በትብብር እንዳዘጋጁትም ተመላክቷል፡፡

በትዕግስት ብርሃኔ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.