ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የመገናኘት የተስፋ ምልክት ሀውልትን ማፍረሷ ተሰማ
አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሁለቱ ኮሪያዎች በሰላም መገናኘት እንደማይችሉ ከተናገሩ ከቀናት በኋላ የሀገራቱ የመገናኘት የተስፋ ምልክት የሆነው ሀውልት መፍረሱ ተሰምቷል፡፡
በኮሪያ ባሕረ ሰላጤ ያለው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በፈረንጆቹ 2000 የተገነባው የዳግም ውህደት ሀውልት ከሳተላይት ምስሎች መጥፋቱም ተመላክቷል።
ይሁንና ሀውልቱ መቼ እና እንዴት እንደተወሰደ የተገለጸ ነገር አለመኖሩም ነው የተገለጸው፡፡
ኪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚያደርጉት ጠንከር ያለ ንግግራቸው የኮሪያን የውህደት ሀውልት ሲያነሳሱ እንደነበር ተሰምቷል፡፡
በሀገሪቱ የሕዝብ ጠቅላይ ምክር ቤት ላይ ባደረጉት ንግግርም ደቡብ ኮሪያን እንደ ሀገራቸው ዋነኛ ጠላት ለማንፀባረቅ ከያዙት አዲስ አቋም ተነስተው የሀገሪቱ ህገ-መንግስት መሻሻል አለበት ብለዋል፡፡
ለአስርት ዓመታት የዘለቀውና በይፋዊ ፖሊሲ ሰሜን ኮሪያን ከደቡብ ኮሪያ ጋር ዳግም ስለመዋሃድ አፅንኦት የሚሰጠው ህገ መንግስት ሊሻሻል እንደሚገባ መናገራቸውንም ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የብሄራዊ ዳግም ውህደት በመባል የሚታወቀው የ30 ሜትር ርዝመት ያለው ሀውልት በራስ መተማመንን፣ ሰላምን እና ብሄራዊ ትብብርን እንደሚያመላክት የደቡብ ኮሪያ መንግስት መረጃዎች ያመለክታሉ።