ለውጪ ገበያ ከተላኩ የቁም እንስሣት ከ9 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ 130 ሺህ 237 የቁም እንስሣት ለውጪ ገበያ በመላክ 9 ነጥብ 276 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ለውጪ ገበያ የተላኩት እንስሣትም÷ 127 ሺህ 464 በጎችና ፍየሎች፣ 2 ሺህ 299 ግመሎች እና 474 የዳልጋ ከብቶች መሆናቸውን በሚኒስቴሩ የእንስሣትና እንስሣት ተዋጽኦ ወጪ ንግድ ግብይት ዴስክ ኃላፊ አበበ ታደሠ ገልጸዋል፡፡
የእንስሣቱ መዳረሻም የመን፣ ኦማን፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያ እና ሳዑዲ ዓረቢያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለውጪ ገበያ ከቀረቡት የቁም እንስሣት 9 ነጥብ 276 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን እና የዕቅዱ 81 ነጥብ 2 በመቶ መፈጸሙን አመላክተዋል፡፡
አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በእንስሣት የ106 ሺህ እንዲሁም በገቢ የ1 ነጥብ 51 ሚሊየን ዶላር ብልጫ አሳይቷል ብለዋል፡፡
ከ2014 ተመሳሳይ ወቅት አንጻርም ቢሆን የ 0 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ብልጫ ማሳየቱን ነው የተናገሩት፡፡
በዮሐንስ ደርበው