Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ስሎቬኒያ የፖለቲካ የጋራ ምክክር ለማድረግ መግባባት ላይ ደረሱ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ስሎቬኒያ የፖለቲካ የጋራ ምክክር ለማድረግ መግባባት ላይ መድረሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በዳቮስ እየተካሄደ ከሚገኘው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከስሎቬኒያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ እና የአውሮፓ ጉዳዮች ሚኒስትር ታንጃ ፋጆን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

አቶ ደመቀ ስሎቬኒያ ለአንድ ዓመት የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና በመመረጧ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡

ስሎቬኒያ በቅርቡ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ መክፈቷ ለሁለቱ ሀገራት ቀጣይ ግንኙነት መጎልበት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል፡፡

ቀጣናዊ ጉዳዮችን በተመለከተም በአፍሪካ ቀንድ ስላለው አሁናዊ የሰላም እና ደኅንነት ሁኔታ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን÷ ሰላምን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን መወጣቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ታንጃ ፋጆን በበኩላቸው÷ ስሎቬኒያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ቁርጠኛ መሆኗ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከርም የሁለትዮሽ የፖለቲካ የጋራ ምክክር ለማድረግ መግባባት ላይ መድረሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.