ሩሲያ ለማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የለገሰችው ስንዴ ካሜሩን ደረሰ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ለማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የለገሰችው 25 ሺህ ቶን የዕርዳታ ስንዴ ካሜሩን ዱዋላ ራስ ገዝ ወደብ መድረሱ ተገለጸ።
ካሜሩን ዱዋላ ራስ ገዝ ወደብ ደርሶ የተራገፈው የሰብአዊ ዕርዳታ ስንዴ ተፈጭቶ ዱቄቱ እንዲዘጋጅ እየተደረገ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
ዱቄቱን የማዘጋጀት ተግባር እንደተጠናቀቀም ለማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እንደሚላክ ተነግሯል።
በዱዋላ የሩሲያ የክብር ቆንስላ ጂን ማሪ ቹሳንግ የአፍሪካ መንግስታት ሩሲያን ለአቀራረቧ፣ ላሳየችው አቋም እና ለአሰራር መንገዷ አድናቆታቸውን ገልፀዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ሩሲያ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የአቻ ለአቻ አጋርነት ትስስር ለመለዋወጥ ሀሳብ ማቅረቧንም አንስተዋል።
ባለፈው ሳምንት ለዚምባብዌ የሚደርስ 25 ሺህ ቶን እህል የጫነ መርከብ ሞዛምቢክ ቤይራ ወደብ መድረሱን አያይዘው የጠቀሱት የክብር ቆንስላ ጂም ማሪ ቹሳንግ፤ እህሉ ለዚምባብዌ ከመላኩ በፊት በአግባቡ በከረጢት እንደሚታሸግ መግለጻቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡
50 ሺህ ቶን ነፃ የሩስያ ስንዴ ቀደም ሲል ለሶማሊያ እና ለኤርትራ መድረሱ የተገለፀ ሲሆን ማሊ እና ቡርኪናፋሶም በቅርቡ እንደሚደርሳቸው ተመላክቷል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡ (FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!