Fana: At a Speed of Life!

የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚጠቀስ የቱሪዝም ልማት ነው – አብርሃም በላይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት በሀገር አቀፍ ደረጃ ማሳያ ተደርጎ የተገነባ የቱሪዝም ልማት መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ መንግስት ያሉንን ሃብቶች ለቱሪዝም ዘርፉ በሚመች መልኩ ለማልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ከተመረጡ ስፍራዎች መካከል አንዱ የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መሆኑን ጠቁመው÷ ፕሮጀክቱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል፡፡

የወንጪ ደንዲ አካባቢ ለስፖርት፣ ለመዝነኛና ለጤና እንዲሁም ለሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተመራጭ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት አካባቢውን ከማልማት ባለፈ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደ ማሳያ ተደርጎ የተገነባ የቱሪዝም ልማት ነው ብለዋል።

በቀጣይም ፕሮጀክቱ አዳዲስ ልማቶችን በማካተት ከቱሪዝምና ሌሎች መስኮች የሚኖረውን ተጠቃሚነት እንዲያሳድግ ተደርጎ የተቀረጸ መሆኑን ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ የአካባቢውን ባህልና ትውፊት እንዲሁም የተፈጥሮ ሁኔታ በጠበቀ መልኩ እንደተከናወነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ይህም ስፍራውን ለጎብኚዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ የአካባቢውን የመሰረተ ልማት ችግር በዘላቂነት የቀረፈ መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢው ህብረተሰብም በግንባታው ጊዜና ከግንባታው በኋላ የፕሮጀክቱ ባለቤት እና ተጠቃሚ ሆኖ እንዲሳተፍ ተደርጓል ነው ያሉት።

በዚህም የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው በ22 ዘርፎች ስልጠና ወስደው ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.