Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል መጽሐፍት ለትምህርት ቤቶች መሰራጨታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ጋር የተጣጣሙ መጽሐፍት በሐረሪ ክልል ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ማሰራጨት መቻሉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

የታተሙ የመማሪያ መጽሐፍት ተማሪዎች በአግባቡና በጥንቃቄ ሊይዙ እንደሚገባ በቢሮው የስርዓተ ትምህርት እቅድና ግምገማ ዳይሬክተር ከማል አብዱልባሲጥ ተናግረዋል።

ቢሮው በክልሉ የመማር ማስተማር ተግባራትን በተሳለጠ መልኩ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ገልጿል።

በክልሉ ለሁሉም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ መጽሐፍት ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለም ተጠቅሷል፡፡

ለግል ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ሽያጭን በማስቀረት የመጽሐፍቱን 20 በመቶ ብቻ ከፍለው የሚወስዱበት ሁኔታ እንደተመቻቸ ተገልጿል፡፡

ተማሪዎች የወሰዷቸውን የመማሪያ መጽሐፍት በአግባቡ መያዝና በተገቢው መልኩ መጠቀም እንዳለባቸውም መገለጹን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡

በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለስኬቱም የትምህርቱ ማህበረሰብ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠይቋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.