የኩላሊት ጠጠር በአብዛኛው እነማንን ያጠቃል? ሕክምናስ አለው?
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኩላሊት ጠጠር በኩላሊት ውስጥ የሚገኝ ከአሸዋ ቅንጣት እስከ የጎልፍ ኳስ ያህል መጠን ሊኖረው የሚችል እና መደበኛ ያልሆነ ቅርጽ ያለው ጠንካራ ክምችት (ክሪስታል) መሆኑ ይነገራል፡፡
• የኩላሊት ጠጠር ምንድን ነው?
እንደ ሕክምና ባለሙያዎች ገለጻም÷ ጠጠሮቹ ከሚኒራል፣ ዓሲድ እና ጨው የተሠሩ ጠንካራ የጠጠር ክምችቶች ናቸው፡፡
የኩላሊት ጠጠር በሽንት ቱቦ ውስጥ ከገባ የሽንትን የፍሰት ሂደት በመዝጋት ኩላሊቱን እንዲያብጥ በማድረግ የሽንት ቱቦው እንዲተነፍስ ሊያደርግ እንደሚችልምያብራራሉ፡፡
ይህም ከባድ ህመም እንደሚያስከትል ነው የሚገልጹት፡፡
• ለመሆኑ የኩላሊት ጠጠር መንስዔ ምንድን ነው?
ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደት፣ አጋላጭ የጤና እክል እና አንዳንድ መድኃኒቶች ከብዙ የኩላሊት ጠጠር መንስዔዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
ከፍተኛ መጠን ያለው ፕሮቲን እንዲሁም ጨው እና ስኳር የበዛባቸው ምግቦችን አብዝቶ መጠቀም፣ በቂ ፈሳሽ አለመውሰድ ለኩላሊት ጠጠር መፈጠር በምክንያትነት ይነሳሉ፡፡
• የኩላሊት ጠጠርን እንዴት መከላከል ይቻላል?
የኩላሊት ጠጠር እንዳይፈጠር ለመከላከል የአመጋገብ ለውጥን ጨምሮ መደረግ ያለባቸው በርካታ ጥንቃቄች እንዳሉ ይታመናል፡፡
ለአብነትም÷ 3 ሊትር ውሃ በመጠጣት የሚወገደውን የሽንት መጠን 2 ነጥብ 5 ሊትር እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ ይመከራል፡፡
በተጨማሪም የአመጋገብ ባሕልን ማስተካከል ( ለምሣሌ፡- የጨው መጠንና የፕሮቲን መጠናቸው የበዛባቸው ምግቦችን አለመመገብ፣ አትክልትና ፍራፍሬን መመገብ፣ የሥጋ ፍጆታን መቀነስ፣ በቂ ካልሺየም ያላቸውን ምግቦች መመገብ) የሚሉት የኩላሊት ጠጠርን ለመከላከል ከሚረዱት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
• የኩላሊት ጠጠር ተጋላጮች እነማን ናቸው?
ተጋላጭነትን በተመለከተ ከጾታ አንጻር በአብዛኛው በወንዶች ላይ እንደሚከሰት ነው ባለሙያች የሚያስረዱት፡፡
በአጠቃላይ በጎልማሳነት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎችን እንደሚያጠቃም ይገለጻል፡፡
• የኩላሊት ጠጠር ህመም ምልክቱ ምንድን ነው?
በአብዛኛው የኩላሊት ጠጠር ምልክት ሳያሳይ መቆየት የሚችል የህመም ዓይነት እንደሆነ ይገለጻል፡፡
ጠጠሩ ከተከሰተ በኋላ ግን ከኩላሊት ተነስቶ በሽንት ማስወገጃ ቱቦ በኩል በሚኖር ሂደት ህመም ስለሚፈጥር ምልክቶች መታየት እንደሚጀምሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በአጠቃላይ የዘርፉ ባለሙያች የጋራ ካደረጓቸው ምልክቶች መካከል÷ ከፍተኛ የጎን ህመም ስሜት መኖር፣ ከጎድን አጥንት በታች የጀርባ ሕመም፣ ወደ ንፍፊትና ወደ ታችኛው የሆድ ክፍል ከፍተኛ ህመም መሰማት፣ ሽንት በሚወገድበት ወቅት የህመም ስሜት መኖር፣ የሽንት ቀለም መለወጥ (ቀይ፣ ቡኒ ወይንም ሮዝ መሆን) የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
በተጨማሪም የደፈረሰ እና መጥፎ ጠረን ያለው ሽንት መኖር፣ አጣዳፊ የሽንት መኖርና ከሌላው ጊዜ በተለየ መብዛት የሚሉት የህመሙ ምልክቶች እንደሆኑ ይገለጻል፡፡
በኩላሊት ጠጠር ምክንያት የሚከሰት ህመም የጠጠሩን እንቅስቃሴ ተከትሎ ቦታውን ሊቀያይር እንደሚችልም ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት፡፡
ከላይ የተገለጹት የተለመዱ የኩላሊት ጠጠር ምልክቶች ሲሆኑ፥ በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ የህመም ስሜት ካለ፣ ከፍተኛ የየውጋት ስሜት ሲኖር፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ ከተከሰተ፣ ትኩሳትና ብርድ ብርድ የማለት ስሜት ሲፈጠር፣ ደም የቀላቀለ ሽንት ሲስተወልና ሽንት ለማስወገድ የመቸገር ሁኔታ ሲከሰት በአፋጣኝ ወደ ሕክምና መሄድ ይመከራል፡፡
• የኩላሊት ጠጠር ሕክምና አለው?
የኩላሊት ጠጠር ሕክምና እንዳለው ባለሙያዎች ያረጋግጣሉ፡፡
ሕክምናው ግን እንደጠጠሩ ዓይነት እና መጠን እንደሚለያይም ነው ከሄልዝ ላይን ያገኘነው መረጃ የሚያመላክተው፡፡