በመዲናዋ በተካሄደ ኦፕሬሽን ከ5 ሺህ 536 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደ ኦፕሬሽን ከ5 ሺህ 536 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ በመዲናዋ ከታኅሣስ 6 እስከ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የኦፕሬሽን ሥራ መካሄዱን አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ወቅትም ከ1 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ከበርካታ ልዩ ልዩ ኤግዚቢቶች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እና በየጊዜው የደረሱበትን ውጤት እየገመገሙ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ነበር፡፡
በዚህ መሰረትም ለ2ኛ ሣምንት ያካሄዱትን የተቀናጀ ኦፕሬሽን ውጤት በመገምገም ሕብረተሰቡ በሰላም ወቶ እንዳይገባ የሚያውኩ የዝርፊያ፣ ቅሚያ እና ተያያዥ ወንጀሎች በተመለከተ በከተማ ደረጃ የተሰሩ ስራዎችን አስመልክተው የቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረ/ኮሚሽነር አድማሱ ኢፋ መግለጫ ሰጥተዋል።
ረዳት ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው÷የቅሚያ ወንጀል በተሽከርካሪና በአካል፣ ወንጀል የሚጠነሰስባቸው ስፍራዎች እና ቤቶች፣ በተባባረ ክንድ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የቁማር ቤቶች 1 ሺህ 114፣ ከታሸጉ ሺሻ ቤቶች 176፣ በመኖሪያ ቤቶች 73 ኪሎ ግራም አደንዛዥ ዕፅ፣ ህፃናትን በመሰብሰብ የተለያዩ አልባሌ ተግባራትን የሚያስፋፉ እና ትውልድ የሚያጠፉ፣164 ህፃናትን ሰብስበው ድርጊቱን ሲፈፅሙ የነበሩ አካላት ዕጅ ከፍንጅ ተይዘዋል ብለዋል።
በተመሳሳይ ሕገ-ወጥ የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ዝውውርን በተመለከተ የየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አለማየሁ አያልቄ እንደገለጹት÷መገናኛ አካባቢ እና ተርሚናል ዙሪያ በተሠራው ዘመቻ ከ190 በላይ ሞባይሎች በኤግዚቢትነት ተይዘዋል።
ከሌሎች ጊዜያት በተለየ ግለሰቦች ቤት ተከራይተው ከ181 በላይ ሲም ካርድ በመያዝ ከባንክ ጋር ባላቸው ግንኙነት ወደ ተለያዩ ሥልኮች እየደወሉ የማጭበርበር ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ግለሰበፐች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም 189 ኩንታል ባዕድ ነገር ቀላቅለው ለሕብረተሰቡ ሊያከፋፍሉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው የማጣራት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ በከተማ ደረጃ በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 5 ሺህ 536 ወንጀለኞች በቁጥጥር ሥር ውለው የማጣራት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በመራኦል ከድር