በቀጣይ 6 ወራት በ77 ከተሞች አዳዲስ የገበያ ማዕከላትን ለማቋቋም ይሠራል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በቀጣይ ሥድስት ወራት በ77 ከተማ አስተዳደሮች እንደ አቅማቸው አዳዲስ የገበያ ማዕከላትን ለማቋቋምና ለማደራጀት እንደሚሠራ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡
ቢሮው ከሰሜን ሸዋ ዞን እና ደብረ ብርሃን ከተማ ከሚገኙ ባለ ድርሻ አካላት ጋር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በተዘጋጀ የ6 ወራት ንቅናቄ ዕቅድ ላይ ተወያይቷል።
የቢሮው ኃላፊ ኢብራሒም መሐመድ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት÷ አሁን እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ለመግታት ሕገ-ወጥ የንግድ አካሄድና የግብይት ሠንሠለት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ መፍታት ወሳኝ ነው፡፡
በተጨማሪም ምርትን ማሣደግ ፣ ዘመናዊ እና ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት መገንባት እንዲሁም በግብይት ሠንሠለት ላይ ያሉ ተዋናዮችን መለየት ላይ በጋራ በመሥራት የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በቀጣይም÷ ያጠረ የገበያ ሠንሠለትን ለመፍጠር እና ሕገ-ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡
እንዲሁም ለሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተዘዋዋሪ በጀት ማመቻቸት እና በ77 ከተማ አስተዳደሮች እንደ አቅማቸው አዳዲስ የገበያ ማዕከላትን ማቋቋምና ማደራጀት በቀጣይ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በግርማ ነሲቡ