Fana: At a Speed of Life!

በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚያደርጉት ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚያደርጉት ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን በልዩ ልዩ የዓለም ክፍል የሚገኙ የኢፌዴሪ ሚሲዮኖች ገለጹ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) በቀረበው ጥሪ መሰረት በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚያደርጉትን ጉዞ በተመለከተ ከኢፌዴሪ ሚሲዮኖች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርትኳን አያኖ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ÷ሚሲዮኖች ከዚህ በፊት በተካሄዱ ሀገራዊ ጥሪዎች የማስተባበር ልምድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ጥሪ ለማስተባበር የጀመሯቸውን ስራዎች አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ (ዶ/ር ) በበኩላቸው÷ ጥሪውን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የሚኖራቸው ቆይታ መልካም እንዲሆን የሚያስተባብሩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው በመስራት ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።

አክለውም ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ዓላማዎችን የሰነቁ፣ በዘርፍና በዕድሜ እርከን የተከፋፈሉ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ጥሪዎችን እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል፡፡

ከማዕከል እስከ ሚሲዮን በሚደረገው የተደራጀ ንቅናቄም የጥሪውን ዓላማ ለማሳካት ይሰራል ማለታቸውን የአገልግሎቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

የሚሲዮን መሪዎችም÷ እንዳሉበት ሀገር ሁኔታ በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው የሚያደርጉትን ጉዞ ለማስተባበርና ስኬታማ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.