Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚሰሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አቶ ሙስጠፌ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕብረተሰቡን ከተረጂነት በማላቀቅ የሥነ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ገለጹ፡፡

ግብርናውን ለማዘመን የተዘጋጀ የሽግግር እቅድ የትግበራ መርሐ ግብር በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን ጎዴይ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እና የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አይሻ መሃመድ ተገኝተዋል፡፡

በዚህ ወቅት አቶ ሙስጠፌ እንዳሉት÷የሶማሌ ማህበረሰብ በግብርና በተለይም በእንሰሳት ሃብት የሚታወቅ ቢሆንም ሰፊ ያልለማ መሬት እና ከፍተኛ የውሃ አቅም አለው ።

ከለውጡ በኋላ ግብርናውን ለማዘመን እና መካናይዝድ ለማድረግ በርካታ ተግባራት የተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው÷በክልሉ የእርሻ ምርታማነትን እና የእንሰሳት ሃብትን በእጥፍ ለማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

አሁን ላይ በክልሉ በመስኖ መልማት ከሚችለው 10 ሚሊየን የሚጠጋ መሬት 850 ሺህ ሄክታር ብቻ እየለማ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

በሚቀጥሉት ዓመታት ግብርናውን በማዘመን በእጥፍ ማልማት ቢቻል ህብረተሰቡን ከተረጂነት በማላቀቅ የስነ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የውጭ ምንዛሬን ለማጎልበት ጉልህ ሚናን ይጫወታል ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ግብርናን ለመለወጥ እና መዋቅራዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ሜካናይዝድ የግብርና ዘዴ መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የሽግግር እቅድ እና የድርጊት መርሐ ግብር በሶማሌና በአፋር ክልል ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) ÷ በምዕራብ እና ደቡብ ጎዴ ላይ 27 ሺ ሄክታር መሬት ማልማት የሚችል የመስኖ ግንባታ እየተከናወነ እንደሆነ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.