ዋሺንግተን ለዩክሬን የአመቱን የመጨረሻ ወታደራዊ ድጋፍ ጥቅል ይፋ አደረገች
አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 18 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዋሺንግተን ለዩክሬን የምታደርገውን የአመቱን የመጨረሻ ወታደራዊ ድጋፍ ጥቅል ይፋ አደረገች።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ኪዬቭ ተጨማሪ የ250 ሚሊየን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ከአሜሪካ እንደምታገኝ ይፋ አድርገዋል።
ወታደራዊ ድጋፉ የአየር መቃወሚ፣ ሮኬት፣ 155 እና 105 ሚሊ ሜትር ተተኳሾች፣ ፀረ ተሽከርካሪ እና ፀረ ታንክ መሳሪያዎች እንዲሁም ከ15 ሚሊየን በላይ መለስተኛ እና አነስተኛ መሳሪያ ተተኳሾችን ያካተተ መሆኑን የዘ ናሽናል ኒውስ ዘገባ ያመላክታል።
የአሁኑን ወታደራዊ ድጋፍ ጥቅል ይፋ መሆን ተከትሎ ግን በኮንግረስ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ልዩነት መፈጠሩ ነው የተሰማው።
የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆኑ ሪፐብሊካኖችም ዋሺንግተን በሜክሲኮ ድንበር ጥብቅ የስደተኞች መቆጣጠሪያ ደንብ ሳታዘጋጅ ይህን መሰሉን ድጋፍ ማድረጓ አግባብ አይደለም በሚል ተቃውመዋል።
በአንጻሩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለገባችው ጦርነት እገዛ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው በማለት ለዩክሬን ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ጥቅምት ወር ለዩክሬን የሚውል የ60 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ይጸድቅላቸው ዘንድ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጅ ይህ ጥያቄያቸው እስካሁን በህግ አውጪዎች ያልጸደቀ ሲሆን፥ ከሁለቱ የምክር ቤት አባላትም ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።
#US #Ukrain
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!