Fana: At a Speed of Life!

በውጭ ለሚኖሩ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በቱሪዝም ሚኒስቴር የሚመራ ዐቢይ ኮሚቴ ወደ ስራ ገባ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)በውጭ ለሚኖሩ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በቱሪዝም ሚኒስቴር የሚመራ ዐቢይ ኮሚቴ ወደ ስራ መግባቱ ተገለጸ።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በሰጡት መግለጫ፥ የመርሐ ግብሩ ዓላማ የትውልድ ቅብብሎሹ እንዲኖርና ከአሁኑ ጀምሮ የወላጆቻቸውን እና የእነሱም መገኛ የሆነችውን ሀገር እንዲያውቁ ማስቻል ነው ብለዋል።

ጥሪውን ተቀብለው ሲመጡም ታሪካቸውንና ባህላቸውን የሚያውቁ ሲሆን÷ እነሱም ሀገራቸውን ባላቸው አቅም እንዲጠቅሙ ያስችላቸዋል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

በዚህ መሰረትም ያወቋትን ሀገራቸውን በማስተዋወቅ የቱሪዝም ዘርፉን እንዲደግፉና የሀገራቸው አምባሳደር እንዲሆኑም እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል።

መርሐ ግብሮቹ የተዘጋጁት ሶስት የእረፍት ጊዜያትን ታሳቢ በማድረግ ሲሆን÷ የመጀመሪያው ከብዝሃ ባህል መሰረትዎ ጋር ይተዋወቁ በሚል መሪ ሃሳብ ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ነው ተብሏል፡፡

በመርሃ ግብሩ ታሪካቸውን ባህላቸውን እንዲያውቁና የእርስ በርስ ትስስርም እንዲፈጠር የሚደረግ ሲሆን÷ የተለያዩ ዝግጅቶችም እንደሚቀርቡ ተጠቅሷል፡፡

‘ታሪካዊ መሰረቶን ይወቁ’ በሚል ደግሞ ሁለተኛ ዙር መርሐ ግብር ከየካቲት 20 እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል ነው የተባለው።

በዚህም ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የቀደምት አባቶችና አያቶቻቸውን ታሪክ እና ማንነታቸውን እንዲያውቁ የሚደረግበት እንደሚሆን ተገልጿል።

ሶስተኛው መርሐ ግብር አሻራዎን ያኑሩ የእረፍት ጊዜዎን ያጣጥሙ በሚል ከሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡

በዚህ መርሃ ግብር ላወቋት ሀገራቸው የበኩላቸውን የሚያደርጉበትና እና በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉ የሚደረግበት ነው ተብሏል።

የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ ጥሪውን በመቀበል ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ የጠየቀ ሲሆን÷ በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሚመጡበት ጊዜ በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዲያስተናግዷቸው ጥሪ አስተላልፏል፡፡

ጥሪውን ተቀብለው ለሚመጡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ትኬት ቅናሽ እንደሚደረግላቸውም ተገልጿል፡፡

ሆቴሎች፣ አስጎብኝ ድርጅቶች የትራስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎች ልዩ የዋጋ ቅናሽ አድርገው ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውም ተጠቁሟል፡፡

የተቀላጠፈ የጉምሩክና ኢሚግሬሽን አገልግሎቶች ለመስጠት የሚያችሉ ሁኔታዎችም ተመቻችተዋል ተብሏል፡፡

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.