Fana: At a Speed of Life!

የከተሞች ፎረም ከተሞች ወደሚፈለገዉ የብልፅግና መንገድ እንዲደርሱ የማድረግ ዓላማ አለው – ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተሞች ፎረም ከተሞች ወደሚፈለገዉ የብልፅግና መንገድ እንዲደርሱ የማድረግ ዓላማ አለው ሲሉ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

የዘንድሮ የከተሞች ፎረም “የዘመኑ ከተሞች ለኢትዮጵያ ብልፅግና” በሚል መሪ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ ከየካቲት 9 እስከ የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ፎረሙን አስመልክቶ ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በሰጡት መግለጫ፤ ፎረሙ የተዘጋጀው በሚኒስቴሩና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትብብር መሆኑን ገልጸዋል።

በፎረሙ ከ150 በላይ ከተሞች፣ ከ20 በላይ ድርጅቶች እንዲሁም ከ20 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሏል።

ፎረሙ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ የከተሞች ፈጣን ዕድገት ቅኝት የሚደረግበት ነዉ ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡

ዘርፉን ከፍ የሚያደርጉና ከተማ ልማት ላይ ሚና ያላቸዉን አካላት በማስተባበር ከተሞችን ወደሚፈለገዉ የብልፅግና መንገድ እንዲደርሱ የማድረግ ዓላማ እንዳለዉም ነው የገለጹት።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ብርሃኑ ዘዉዴ በበኩላቸዉ÷ ከክልል ጀምሮ እስከዞን ድረስ የተዋቀረ ኮሚቴ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ለፎረሙም 25 ነጥብ 55 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ የተለያዩ መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

ፎረሙ በሚካሄድበት ወላይታ ሶዶ ከተማ እንግዶች በሠላም ቆይተው በሰላም እንዲመለሱ ለጸጥታ ሥራዎች ልዩ ትኩረት መሰጠቱም ተመልክቷል።

ምንተስኖት ሙሉጌታ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.