Fana: At a Speed of Life!

በእርግዝና ወቅት ፍራፍሬ የመመገብ አስፈላጊነት

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በእርግዝና ወቅት ፍራፍሬን መመገብ በርካታ ጥቅሞችን እንደሚሰጥ በዘርፉ የተካሄዱ በርካታ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

በእርግዝና ወቅት የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ፅንሱ ጤናማ ሆኖ በሚፈለገው መጠን እንዲያድግና የእናት ጤንነትም እንዲጠበቅ ስለሚያግዝ ፋይዳው የጎላ ነው ፡፡

ነፍሰ ጡር እናቶች በፋይበር፣ ፖታሺዬም፣ ቫይታሚን ኤ እና ሲ፣ በፎሊክ አሲድ እና በሌሎች ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ምግቦችን እንዲመገቡ የሚመከር ሲሆን÷ ፍራፍሬዎች ደግሞ ዋነኛ ምንጮች ናቸው፡፡

ፍራፍሬ በእርግዝና ጊዜ በተለያየ ሰዓት በመክሰስ፣ ከምግብ በኋላ፣ ሌሊት ላይ ፣ በጠዋት እና መኝታ ሰዓት ሊወሰድ ይችላል፡፡

በእርግዝና ጊዜ ከሚመከሩ የፍራፍሬ አይነቶች መካከል ብርቱካን፣ ሙዝ ፣ አቮካዶ፣ ሎሚ፣ ማንጎ፣ አፕል፣ ሀባብ፣ እንጆሪ፣ ሸክኒት፣ አፕሪኮት፣ የወይን ፍሬ፣ መንደሪን፣ ዘይቱን፣ ቴምር፣ ኮክ፣ የበለስ ፍሬ ይጠቀሳሉ ፡፡

በተጨማሪም ነፍሰ ጡር ሴት ሮማን ፣ ሆጲ፣ ሊቺ ፣ ኮኮናት፣ ፐርስሞንስ፣ ኔክታሪን እና የባህር ሎሚና የመሰሰሉ ፍራፍሬዎችን ብትመገብ ጠቃሚ እንደሆነ ይመከራል፡፡

ይሁን እንጅ የተጠቀሱትን ሁሉ ፍራፍሬዎች መመገብ የግድ ሳይሆን አቅም በፈቀደ መጠን በአካባቢያችን የምናገኘውን ፍራፍሬ መመገብ አስተማማኝ ለሆነ የጽንስ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ባለሙዎች ይገልጻሉ፡፡

በእርግዝና ወቅት ፍራፍሬ መመገብ የድርቀት ችግር ለመቀነስ፣ የጽንስ ሴሎችን ከጉዳት ለመከላከል፣ የማቅለሽለሽ ችግርን ለመቀነስ፣ ግፊትን ለመከላከል፣ ክብደትን ለመቆጣጠር፣ የጨጓራ ህመምን ለመቀነስ፣ ያለጊዜ ምጥ እንዳይመጣ እንደሚያደርግና ሌሎችም በርካታ ጠቀሜታዎች እንደሚሰጥ ይነገራል፡፡

ፍራፍሬዎች የፎሊክ አሲድ ዋነኛ መገኛ በመሆናቸው ነፍሰ ጡር ሴቶች ቢመገቡ መልካም እንደሆነ የኸልዝ ላይን እና የሜዲካል ኒውስ ቱደይ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.