Fana: At a Speed of Life!

ጥቂት ስለ ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በኮንታ ዞንና በዳውሮ ዞን መካከል የሚገኝ እና በዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት የታደለ ነው፡፡

ብሔራዊ ፓርኩ በ1997 ዓ.ም በኮንታና በዳውሮ ህዝቦችና አስተዳደር አካላት ጥያቄና ተሳትፎ መሰረት በብሄራዊ ፓርክ ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን÷ ፓርኩ የሚያካልለው የቆዳ ስፋት 1 ሺህ 410 ካሬ ኪሎ ሜትር ስኩዌር ነው፡፡

ፓርኩ በመካከለኛው ኦሞ ሸለቆ ውስጥም የሚገኝ እና ከአዲስ አበባ በ475 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ፓርኩ የግዙፉ የአፍሪካ ዝሆን መኖሪያም ሲሆን በውስጡ ከ800 በላይ የሚሆኑ ዝሆንና ከ5 ሺህ በላይ ጎሽ የሚገኙበት መሆኑ ፓርኩን ልዩ ያደርገዋል፡፡

በተጨማሪም 40 ትላልቅና መካከለኛ አጥቢ እንዲሁም 18 ትናንሽ አጥቢ የዱር እንስሳት ዝሪያዎች ይገኛሉ።

በጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ እንደ አጥቢዎቹ ሁሉ የበርካታ የአዕዋፋት ዝርያዎች መኖሪያም ጭምር ነው፡፡

እስካሁን በተጠናው ውስን ጥናት ብቻ 137 የአዕዋፍ ዝርያዎች የተለዩ ሲሆን÷ ከእነዚህም ውስጥ 6ቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡

ፓርኩ በብዙ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቱ የተጠበቀ ፓርክ ነው ያስባለው የእጽዋት ስብጥሩና ደኑ ነው፡፡

እንዲሁም 106 እንጨታማ የእጽዋት ዝሪያዎች የሚገኝበት ሲሆን÷ ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ የእጽዋት ዝርያዎች በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡

በተጨማሪም በውስጡ ከሚገኙ የዱር ዕፅዋት ዝሪያዎች መካከል ዝንጅብል፣ ቡና፣ ኮረሪማ፣ እንሰት፣ እጣንና የጌሾ ዝርያዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በፓርኩ ውስጥ ባሄ፣ ቡሎ፣ ሺታ፣ ቆቃ፣ ከሪቤላና ጮፎሬ የተሰኙ ስድስት አስደናቂና የጎብኚን ቀልብ የሚስቡ ሐይቆች አሉ።

በብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ከሚገኙ ሐይቆች በአንዱ ብርቅዬ ወርቃማ የዓሳ ዝርያ የተገኘ ሲሆን÷ በዓለም ሊቃውንት እውቅና አግኝቶ በሳይንሳዊ ስሙ ጋራ ጨበራ በመባልም ይጠራል፡፡

ሌላኛው ከብሔራዊ ፓርኩ ገፀበረከቶች መካከል ለአብነት ፏፏቴዎች፣ ፍልውሃዎችና የማዕድን ውሃዎች የሚጠቀሱ መሆናቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

 

ብሔራዊ ፓርኩ በአሁኑ ሰዓት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የተጀመረውና ከ2 ቀናት በኋላ የሚመረቀው የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ክላስተር “የዝሆን ዳና ሎጅ” ፕሮጀክትን ይዟል።

ፕሮጀክቱ ቱሪስቶች ብዙም ሳይጉላሉና ሳይለፉ በቀላሉ ጎብኝተው እንዲመለሱ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም ባለፈ ፓርኩን በተገቢው ሁኔታ ለማስተዳደርና የዱር እንስሳትን በቅርበት ለመከታተልና ለመጠበቅ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ነው የተባለው፡፡

ይህ ብሄራዊ ፓርክ በኮንታ እና በዳውሮ ህዝብ ፍላጎት እንደተቋቋመ ሁሉ በጥበቃ ሂደትም ህዝቡ ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል ብሄራዊ ፓርኩን ከተለያዩ ጥፋቶች በመታደግ መልካም ዝና እንዲኖረው አድርገውታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.