Fana: At a Speed of Life!

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ም/ቤት የአንድ አባሉን ያለመከሰስ መብት አነሳ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት እያካሄደው ባለው 6ኛ ዙር 3ኛ አመት የስራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤዉ የአንድ አባሉን ያለመከሰስ መብት አነሳ።

ምክር ቤቱ በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ ባለው ጉባኤው የአንድ የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት ከለላ እንዲነሳ ተወያይቶ ከመወሰን በተጨማሪ በልዩልዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።

ልዩ ልዩ ሹመቶችን ማጽደቅ፣ የመስተዳድር ም/ቤት የ2016 በጀት አመት ዕቅድ ተወያይቶ ማፅደቅ ጉባኤው የሚወያይባቸው አጀንዳዎች እንደሆኑ ተጠቁሟል።

በተጨማሪም÷ የክልሉን ጠቅላይ ፍ/ቤት የ2016 በጀት አመት እቅድ ተወያይቶ ማፅደቅ፣ የክልሉን ም/ቤት የአሰራርና የአባላት ስነ ምግባር ረቂቅ ደንብ ተወያይቶ ማፅደቅ እና ሌሎችም አጀንዳዎች ይገኙበታል።

በመሆኑም ምክር ቤቱ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ በአቶ ታረቀኝ ደግፌ ፊታኔ ላይ ያቀረበውን ያለመከሰስ መብት የማንሳት ጥያቄ በክልሉ ሕገ መንግሥት መሠረት በሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው በኩል ከተመለከተ በኋላ ይህንኑ የተመለከተ የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ ቀርቦ በ7 ተቃውሞ እና በ5 ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

አባሉ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል በመናድ ወንጀል በመጠርጠራቸው ነው ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የተጠየቀው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.