Fana: At a Speed of Life!

ብሪታንያ በታዳጊ ህጻናት የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ገደብ ልትጥል ነው

 

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 6 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሪታንያ በታዳጊ ህጻናት የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ገደብ ልትጥል መሆኑ ተሰማ።

ይጣላል የተባለው ገደብ የታዳጊ ህጻናቱን የአዕምቶ ጤንነት ለመጠበቅ ያለመ መሆኑም ተሰምቷል።

ብሉምበርግን ዋቢ ያደረገው የአር ቲ ዘገባ እንደሚያመላክተው በታዳጊ ህጻናቱ ላይ የሚጣለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቃም በጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ አማካኝነት የቀረበ ነው።

ቲክ ቶክ፣ ትዊች እና ስናፕ ቻትን የመሳሰሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በኢንተርኔት ደህነነት ህጉ አማካኝነት ገደብ ይጣልባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ገደቡ ህጻናቱ ማህበራዊ ሚዲያን ይጠቀሙ ዘንድ የወላጆችን ይሁንታ ማግኘትን እንደሚያካትትም ተገልጿል።

ከልጆች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር በተያያዘም የጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ በዚህ ጉዳይ ላይ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አያይዘውም የታዳጊ ህጻናቱን ደህንነት ለመጠበቅ ቅድሚያ እንደሚሰጥና አሁን ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አለመደረሱን አስረድተዋል።

በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለማሳለፍ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔዎች በቅርቡ ተወያይተው ውሳኔ እንደሚያሳልፉ አር ቲ በዘገባው አስታውሷል።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሃገሪቱ መንግስት ባለፈው ጥቅምት ወር የኦንላይን ደህንነት መጠበቂያ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።

በመመሪያው መሰረት የማህበራዊ ትስስር ገጾች እንደ ሽብርተኝነት እና ወሲብ ቀስቃሽ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በገጻቸው እንዳያስተናግዱና በፍጥነት እንዲያስወግዱ እንዲሁም እድሜ ማረጋገጫ ቴክኖሎጂዎችን እንዲተገብሩ ይደነግገጋል።

ይህን በማያደርጉት ላይ እስከ 17 ሚሊየን ፓውንድ ቅጣት እንደሚጥልም በመመሪያው ላይ ተደንግጓል።

በብሪታንያ በአስር አመት ውስጥ በታዳጊዎች የሚከሰተው የአዕምሮ ጤና መቃወስ እየጨመረ ሲሆን፥ እድሜያቸው ከ8 እስከ 25 ከሚገኙ ብሪታንያውያን መካከል ከአምስቱ አንዱ የዚህ ችግር ሰለባ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ለዚህ ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የዘ ታይምስን ጥናት ዋቢ ያደረገው ዘገባ ያመላክታል።

ጥናቱ የማህበራዊ ሚዲያ አዘውትረው የሚጠቀሙ ታዳጊዎችና ወጣቶች ለሲጋራ ማጨስ፣ ለአልኮል ሱሰኝነት፣ ለአደንዛዥ ዕፅ እና ለአዕምሮ ጤና መቃወስ ችግር እንደሚዳረጉም አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.