Fana: At a Speed of Life!

10 ነጥብ 5 ሚሊየን ሔክታር የደረሰ ሰብል መሰብሰቡ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 10 ነጥብ 5 ሚሊየን ሔክታር መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከበደ ላቀው እንዳሉት÷በመኸር እርሻ ከለማው 17 ነጥብ 5 ሚሊየን ሔክታር መሬት ውስጥ እስካሁ 10 ነጥብ 5 ሚሊየኑ ተሰብስቧል ፡፡

ከዚህ ውስጥም 9 ነጥብ 5 ሚሊየኑ በባህላዊ መንገድ የተሰበሰበ ሲሆን÷ቀሪው ከ800 ሺህ በላይ የሚሆነው ደግሞ በዘመናዊ የግብርና መሳሪያ ኮምባይነር መሰብሰቡን ገልጸዋል ፡፡

ከተሰበሰበው ውስጥ 4 ነጥብ 1 ሚሊየኑ መወቃቱን ጠቁመው ÷ከዚህም 114 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን አቶ ከበደ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ቆላማ እና ወይና ደጋ አካባቢዎች ላይ ምርት የመሰብሰብ ሥራው እየተጠናቀቀ ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው ÷በደጋማ አካባቢዎች ላይ እስከ ጥር ወር ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል ፡፡

ዋና ዋና የሚባሉ እንደ ጤፍ ፣ ስንዴ ፣ማሽላ ፣ገብስ እና በቆሎም በብዛት የተሰበሰቡ ሰብሎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ድህረ ብክነትን ከመከላከል አኳያ በቅድመ ጥንቃቄ ሥራው ለአርሶ አደሩ እና ለግብርና ባለሙያዎች ተከታታይ የግንዛቤ ማሳደግ ስራ ተሰርቷልም ነው ያሉት፡፡

አርሶ አደሮች ምርታቸውን በኮምባይነር እንዲሰበስቡ በእጅ የሚያዙ አነስተኛ የግብርና ቴክኖሎጂ ማጨጃዎችንና አነስተኛ የመውቂያ ሜካናይዜሽኖችን እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑም ተናግረዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.