የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም ፋይናንስ የማሰባሰብ ስራ መጀመሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 3 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ፋይናንስ የማሰባሰብ ስራ መጀመሩን ገለጸ፡፡
የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም እስከ አሁን የተከናወኑ ተግባራትን በማስመልከት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በመግለጫቸው የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ማሰባሰብ ተጀምሯል ብለዋል፡፡
የፋይናንስ ማሰባሰቡ ተግባርም በኮሚሽኑ ፕሮጀክትና በፕሮግራም ላይ ተመስርቶ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ከሀገር ውስጥና ከልማት አጋሮች ፋይናንስ የማሰባሰብ ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
ከፋይናንስ አቅርቦት ማሰባሰብ በተጨማሪ ልዩ ልዩ የዝግጅት ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘገቧል።
የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ስራው ስኬታማ እንዲሆን የክልል መንግሥታት ተሳትፎ አስፈላጊ በመሆኑ ከሚመለከታቸው ክልሎች የሥራ ሃላፊዎች ጋር ምክክሮችን ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።
ለቀድሞ ታጣቂዎች የሥነ-ልቦና እና የሙያ ክህሎት ሥልጠና ለመስጠት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።