በመከላከያው ዘርፍ ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደምትሠራ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር በመከላከያው ዘርፍ በትብብር እንደምትሠራ አስታወቀች፡፡
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አታሼ ኮሎኔል ማርክ ባቫን እንደገለጹት ÷ ሀገራቸው በወታደራዊ ቁሥ አቅርቦት እና በተለያዩ የትብብር መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት እና አቅማቸውን ለማጠናከር ፍላጎት አላት፡፡
የዩናይትድ ኪንግደም ወታደራዊ አታሼዎች የብላቴ የኮማንዶና ዓየር ወለድ ማሠልጠኛ ማዕከልን መጎብኘታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኮማንዶና አየር ወለድ ማሠልጠኛ ማዕከል አዛዥ ኮሎኔል ቦጃ አጋ ÷ ስለ ማሠልጠኛ ማዕከሉ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ እና ሥለ ሥልጠና አሠጣጥ ሂደቱ ለእንግዶች ገለፃ አድርገዋል።
ከመከላከያ ጋር አብረው መሥራት ከሚፈልጉ ሀገራት ጋር በጋራ መስራት ሽብርተኞችን ለማጥፋት እና ተሞክሮን ብሎም ልምድን ለመወራረስ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
በማሰልጠኛ ማዕከሉ የተቀናጀ ስልጠና ለመስጠት ምቹ መሰረተ ልማት እየተገነባ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የዩናይትድ ኪንግደም ወታደራዊ አታሼዎች በማዕከሉ የሚሠጠው የዓየር ወለድ ፣ የልዩ ኃይል እና የፀረ ሽብር ሥልጠና ውስብስብ የሆነ እና ግዳጅን ለመወጣት የሚያስችል እንደሆነ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ኮሎኔል ማርክ ባቫን ዘመናዊ የሥልጠና መሠረተ ልማት መኖሩ ሠልጣኞችን በብቃት እና በጥራት አሠልጥኖ ለማብቃት አጋዥ መሆኑን አሥረድተዋል፡፡