ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ጀምሮ ያለ ቪዛ ወደ ኬንያ መግባት ይቻላል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ማንኛውም ጎብኚ ከመጪው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ጀምሮ ያለ ቪዛ ፈቃድ ወደ ኬንያ መግባት እንደሚችል ተገለጸ፡፡
የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሳሞኢ ሩቶ እንዳሉት÷ አዲሱን ፖሊሲ በሀገሪቷ ለመተግበር የሚያስችል ዲጂታል የኤሌክትሮኒክ መረጃ ምኅዳር ተዘጋጅቷል፡፡
ይህ የኬንያ ውሳኔ የሀገሪቷን ቱሪዝም ዘርፍ እንደሚያነቃቃ ከወዲሁ ተስፋ መደረጉን ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቧል፡፡
ኬንያውያን ከድንበራቸው ባሻገር ከቅርብ የአፍሪካ ሀገራትም ሆነ ከማንኛውም የዓለም ክፍል የሚገቡ ተጓዦችን በደስታ ለመቀበል ዝግጁ ናቸው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡
በመሆኑም ከየትኛውም የዓለም ክፍል ወደ ኬንያ መግባት የሚፈልጉ መንገደኞች የሚጠበቅባቸው አስቀድመው ኤሌክትሮኒክ የጉዞ ፈቃድ ማረጋገጫ ማግኘት ነው፡፡
ኬንያ ፖሊሲዋን ይፋ ያደረገችው በርካታ የዓለም ሀገራት በራቸውን ለተጓዦች ለመክፈት ሁኔታዎችን እያቀለሉ ባሉበት ወቅት ነው፡፡
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ስለ ጉዳዩ ለሕዝቡ በይፋ የተናገሩት በትናንትናው ዕለት በናይሮቢ ኡሁሩ መናፈሻ በተዘጋጀው 60ኛው የኬንያ የነጻነት ቀን በዓል ላይ ነው፡፡