Fana: At a Speed of Life!

የፋይናንሱ ዘርፍ ማሻሻያዎች ጠንካራ የምጣኔ ኃብት እድገት ለማምጣት ወሳኝ መሆናቸው ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፋይናንስ ዘርፍ እየተደረጉ ያሉ ለውጦች ዘላቂና ጠንካራ የምጣኔ ኃብት እድገት ለማምጣት መሠረት እየጣሉ መሆኑን በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሐ-ግብር ከፍተኛ የምጣኔ ኃብት አማካሪ አሊ ዛፋር ገለጹ።

የምጣኔ ኃብት አማካሪው አሊ ዛፋር እንዳሉት÷የመንግሥት ማሻሻያዎች ውድድርን በመፍጠርና አማራጭን በማምጣት ዘላቂና ጠንካራ የምጣኔ ኃብት እድገት ለማምጣት ጥሩ መሠረት እያኖሩ ነው፡፡

የቴሌኮም እና የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት መደረጉ ትልቅ የማሻሻያ እርምጃ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በፋይናንስ ዘርፉ እየተደረጉ ያሉ ዘርፈ-ብዙ የማሻሻያ ሥራዎች ተወዳዳሪ የሚያደርጉ፣ አዳዲስ አሠራሮችን የሚያሰርፁ፣ የገንዘብ አማራጮችን የሚያሰፉና ፈጠራን የሚያበረታቱ መሆኑንም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ለማስጀመር ሥራ መጀመሩም የዘርፉን እድገት የሚያበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በምጣኔ ኃብት ላይ እየተወሰዱ ያሉ ለውጦችና ማሻሻያዎች የታለመላቸውን ግብ እንዲያሳኩ ጥናትን መሠረት ያደረጉ አሠራሮችን መከተል ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የገንዘብ አቅርቦት፣ የሎጂስቲክስ፣ የክህሎትና የመሬት አቅርቦትን በተመለከተ በቀጣይነት ብዙ መሥራት የሚጠይቅ መሆኑንም አብራርተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሪፎርም እውን ለማድረግ በጥናትና ምርምር፣ በፖሊሲ ምክረ-ሃሳብ፣ በዓለም አቀፍ ተሞክሮ፣ አቅም ግንባታና ሌሎች ዘርፎች በቅርበት መሥራቱን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.