ማህበሩ የ7ኛ ሣምንት የዲስፕሊን ውሳኔዎችን ይፋ አድርጓል
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ አክሲዮን ማህበር በ7ኛ ሣምንት ጨዋታዎች የተላለፉ የዲስፕሊን ውሳኔዎችን ይፋ አድርጓል፡፡
በሣምንቱ መርሐ ግብር በተደረጉ ሠባት ጨዋታዎች ስድስቱ በመሸናነፍ እንዲሁም አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ 16 ጎሎች በ14 ተጫዋቾች ተቆጥሯል።
በተጨማሪም 28 ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾችና ቡድን አመራሮች ሲሰጥ ሁለት ቀይ ካርድ ተመዝግቧል።
በተጫዋች እና ቡድን አመራሮች ላይ በተላለፈ ውሳኔ ኦላኒ ሴቄታ(የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድን መሪ) ክለባቸው ከሻሸመኔ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ በ73 ኛ ደቂቃ ላይ ዳኛን አፀያፊ ስድብ በመሳድብ ከጨዋታ ሜዳ መወገዳቸውም ነው የተገለጸው፡፡
ቡደን መሪው ለፈፀሙት ጥፋት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገድና 10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡
ዳግም ንጉሴ(ሀዲያ ሆሳዕና) ክለቡ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ባደረገው ጨዋታ በ 90+2 ኛ ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያስጥ ጥፋት በመፈፀሙ ቀይ ካርድ አይቶ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ለፈፀመው አንድ ጨዋታ እንዲታገድ ተወስኗል፡፡
ቴዎድሮስ በቀለ /ከሀምበሪቾ/ ክለቡ ከወልቂጤ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ያልተመዘገቡ ተጫዋቾች ከተቀመጡበት ቦታ ላይ ሆኖ የውሀ መጠጫ ፕላስቲክ ወደ ሜዳ ስለመወርወሩ ሪፖርት የቀረበበት ሲሆን ፥ ተጨዋቹ ለፈፀመው ጥፋት 25 ሺህ ብር እንዲከፍል ተወስኗል።
በተጨማሪም ለአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ/ሀዋሳ ከተማ-ዋና አሰልጣኝ/ እና አሰልጣኝ ደግያረጋል ይግዛው(ባህር ዳር ከተማ) በ7ኛ ሣምንት ባሳዩት ያልተገባ ባህሪ የፕሪምየር ሊግ ውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ለማነጋገር ጥሪ ማድረጉን አስታውቋል።