Fana: At a Speed of Life!

በቢሾፍቱ እየተገነባ ያለው የባህር ሀይል መሰረታዊ ባህረኞች ማሰልጠኛ በዕቅዱ መሰረት ይጠናቀቃል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቢሾፍቱ እየተገነባ ያለው የባህር ሀይል መሰረታዊ ባህረኞች ማሰልጠኛ በዕቅዱ መሰረት እንደሚጠናቀቅ ተጠቆመ።

በመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ የተመራ ልዑክ በቢሾፍቱ እየተገነባ የሚገኘውን የባህር ሀይል መሰረታዊ ባህርኞች ማሰልጠኛ የግንባታ ሂደት ጎብኝቷል፡፡

ጄኔራል መኮንኖቹ ፕሮጄክቱን ተዘዋውረው ከጎበኙ በኋላ ስለ ግንባታው ሂደት በግንባታው ተቆጣጣሪ መሃንዲስ ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡

ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ ዋና መምሪያ ግንባታውን በተመደበለት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ውል በተገባው መሰረት እስካሁን 10 ወር መጠቀሙንና ግንባታውም በተፋጠነ ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሬር አድሚራል ናስር አባዲጋ በበኩላቸው እንደገለጹት÷ የመሃንዲስ ዋና መምሪያው አሁን በያዘው ፍጥነትና ከቀጠለ ከተቀመጠለት ጊዜ ባነሰ ግንባታውን አጠናቆ እንደሚያስረክብ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ማሰልጠኛው በመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምርያ እየተገነባ መሆኑን “ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የባህር ሃይል መሰረታዊ ባህርተኞች ማሰልጠኛ ተቋም በ10 ወራት ውስጥ የግንባታ ሂደት ከ25 ከመቶ በላይ አፈፃፀም ላይ መድረሱም ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.