የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች መሪ ለፕሬዚዳንት ፑቲን አቀባበል አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ሀገራቸው ለገቡት የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በፈረንጆቹ ከ2019 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች አቡ ዳቢ ገብተዋል።
ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው በሁለትዮሽ ግንኙነት እና በመካከለኛው ምስራቅ ስላለው ሁኔታ እንደሚወያዩ ክሬምሊን አስታውቋል፡፡
በስብሰባቸው መጀመሪያ ላይ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ፕሬዚዳንት ፑቲንን “ውድ ጓደኛዬ” በማለት እንደጠሩና የሩስያ አቻቸውን እንደገና በማግኘታቸው ደስተኛ እንደሆኑ መናገራቸው ተገልጿል።
ሁለቱ መሪዎች ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መሪ በክብር እንግድነት በተገኙበት በሴንት ፒተርስበርግ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ መገናኘታቸው ተጠቅሷል።
ፑቲን በቅርቡ በሞስኮ እና በአቡ ዳቢ መካከል ያለው ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ መድረሱን አመልክተዋል፡፡
ይህም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በአረቡ ዓለም የሩሲያ ትልቋ የንግድ አጋር እንደሆነች መናገራቸው ተመላክቷል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወታደራዊ ጄቶች የፑቲንን መምጣት ምስራች ለማብሰር የሩስያን ሰንደቅ ዓላማ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ሰማይ ላይ ማሳየታቸው ተገልጿል።
ግመል ጋላቢዎች እና በፈረስ ላይ የተጫኑ መኮንኖች ፑቲን ከአውሮፕላን ማረፊያ ወደ ፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግስት በሞተረኞች ታጅበው ሲያቀኑ እጅ ሲነሱ እንደነበር አር ቲ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!