በዱባይ 136 ሚሊዮን ዶላር የተሸጠው 3ኛው የዓለማችን ቅንጡ አፓርታማ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዱባይ ፓልም ጁሜራህ በተባለው ሰው ሰራሽ ደሴት አካባቢ የሚገኘው አፓርታማ 136 ሚሊዮን ዶላር በሆነ ዋጋ በመሸጥ የሀገሪቱን የሪል ስቴት ሽያጭ ሪከርድን ሲሰብር በዓለም አቀፍ 3ኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ለ20 ዓመታት በሪል ስቴት ልማት ዘርፍ በተሰማራው ኮሞ ሬዚደንስ የሪል ስቴት አልሚ ድርጅት የተሰራው ይህ አፓርታማ በዱባይ ከሚገኙ እጅግ በጣም ውድ ህንፃዎች ቀዳሚ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡
አፓርታማው የሚገኝበት ደሴት 560 ሄክታር ስፋት፣ 52 ፎቆች፣ እና 232 ሜትር እርዝመት ያለው ሲሆን 80 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
በዱባይ አዲሱ የቱሪስት መስህብ የሆነው ይህ ደሴት የተለያዩ ሆቴሎች እና የግል መኖሪያ ቤቶች ያሉት ሲሆን የዱባይ የባህር ዳርቻዎቸን 360 ዲግሪ ተዘዋውሮ ለማየት የሚያስችሉ ሰገነቶችም አሉት ተብሏል፡፡
ኮሞ ሬዚደንስ እንዳስታወቀው÷ የቅንጡ አፓርታማው ግንባታ በ2027 ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለገዥዎቹ ርክክብ ይደረጋል ማለቱን ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡
ቀደም ሲል በዱባይ ማርሳ አል አራብ ሆቴል ውስጥ የሚገኘው አፓርታማ 114 ሚሊዮን ዶር በመሸጥ የሪል ሰቴት ሽያጭ ሪከርድን ይዞ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
አፓርታማው በዓለም አቀፍ የህንፃዎች ሽያጭ 3ኛ ደረጃን ሲይዝ በእንግሊዝ ለንደን የሚገኘው ሐይድ ፓርክ አፓርታማ 237 ሚሊዮን ብር በማውጣት 2ተኛ እንዲሁም በፈረንሳይ ሞናኮ የሚገኘው ኦዲዮን ታወር 437 ሚሊዮን ዶላር በመሸጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል፡፡