Fana: At a Speed of Life!

በታንዛኒያ በመሬት መንሸራተት 47 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ተሰማ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜናዊ ታንዛኒያ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ 47 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡

አደጋው በከባድ ዝናብ ምክንያት የተከሰተ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡

ሰሜናዊ ታንዛኒያ ገዥ ጃኔት ሚያንጃ÷ በኬቲሽ እና ዶዶማ ከተሞች በጣለው ከባድ ዝናብ መተላለፊያ ድልድዮች በደለል መሞላታቸውን እና በተቆራረጡ ዛፎች እና ድንጋዮች መዘጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈው ምስል ላይ በርካታ ቤቶች እና መኪኖች በጎርፍ ተውጠው ተስተውለዋል፡፡

በአደጋው ለህልፈት ከተዳረጉት በተጨማሪ 85 ሰዎች መጎዳታቸውም ነው የተነገረው።

በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የታንዛኒያዋ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን÷ በተከሰተው አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀው በአካባቢው የመንግስት ነፍስ አድን ሰራተኞች እንዲሰማሩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቃው የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ለሳምንታት ‘ከኤል ኒኖ’ ክስተት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ውሽንፍር አዘል ዝናብ እና ከባድ ጎርፍ እየተጠቃ መሆኑን ዘ ኔሽን ዘግቧል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም በሶማሊያ ከሚሊየን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ነው ዘገባው ያመላከተው።

ዓለም ላይ ለሙቀት መጨመር መንስኤ የሆነው ‘ኤል ኒኖ’ የአየር ንብረት ክስተት በአንዳንድ አካባቢዎች ለድርቅ መከሰት መንስኤ ሲሆን፥ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ከባድ ዝናብ ያስከትላል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.