Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የሥርዓተ- ምግብ ሽግግርን የሚያሳካ ተሞክሮ በኮፕ28 አቅርባለች- ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በኮፕ 28 ጉባዔ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችልና የሥርዓተ- ምግብ ሽግግር አጀንዳን የሚያሳካ ተሞክሮ ማቅረቧን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በዱባይ እየተካሄደ የሚገኘውን የኮፕ 28 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በተመለከተ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም÷ በዱባይ እየተካሄደ የሚገኘው የኮፕ 28 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ጉባዔዎች አዲስ አጀንዳ ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።

ይህም ሰፊ ለውጥ ማምጣት የሚችለው የሥርዓተ- ምግብ ሽግግርን ማረጋገጥ ሲቻል በመሆኑ በጉባዔው መካተቱ ለዘርፉ ለውጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በሌላ በኩል በኮፕ ጉባዔዎች የሚወሰኑ ጉዳዮች አፈጻጸም እንደ ችግር እንደሚነሳ ገልጸው÷ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳዎችን የሚያሳኩ የድርጊት መርሐ-ግብሮች ቀርጻ በጉባዔው መሳተፏን ገልጸዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በቀዳሚነት ወደ ትግበራ ይዛ የገባችውን የድርጊት መርሐ-ግብሮች በጉባዔው ማስተዋወቋን ነው ገለጹት።

የአየር ንብረት ለውጥ አማቂ ጋዞችን መቀነስና መቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች ማስተዋወቋንም አውስተዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርም እስከ 2026 ድረስ 50 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እስካሁን 32 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን አስረድተዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ በራሷ ዐቅም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያከናወነች የሚገኘውን ሥራ ለዓለም በተሞክሮ ማካፈሏን ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡

በግብርናው ዘርፍ የዓየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል የስንዴ ምርት ዘዴን በጉባዔው በተሞክሮነት ማሳየቷንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የስንዴ ምርቱ በራስ ዐቅም በክረምትና በበጋ የሚከወን ተሞክሮ መሆኑን በማውሳት÷ በአፍሪካ ደረጃ በዚህ ዓመት በቀዳሚ አምራችነት ኢትዮጵያ የምትነሳበት እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህም ለብዙ ሀገሮች ልምድና ተሞክሮ እንደሚሆን እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

በእንስሳት ሀብት ዘርፍም የሌማት ትሩፋትን በመጠቀም የመጣውን ለውጥ በጉባዔው እንደ ተሞክሮ ማሳየት እንደተቻለም ነው የገለጹት፡፡

በጉባዔው የተነሳውን አጀንዳ ከማሳካት አንጻር ኢትዮጵያ የዓየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችልና የሥርዓተ-ምግብ ሽግግርን አጀንዳ የሚያሳካ ተሞክሮ ማከፈሏን ነው ያስረዱት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.