ደቡብ ኮሪያ የመጀመሪያዋን የስለላ ሳተላይት ወደ ህዋ አመጠቀች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ ኮሪያ የመጀመሪያዋን ወታደራዊ የስለላ ሳተላይት በተሳካ ሁኔታ ወደ ህዋ ማምጠቋን አስታወቀች፡፡
ሴኡል የስለላ ሳተላይቷን ያመጠቀችው ጎረቤቷና ባላንጣዋ ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ወታደራዊ የስለላ ሳተላይት ወደ ህዋ ማምጠቋን ተከትሎ ነው፡፡
ሀገራቱ በዘርፉ የጀመሩት ፉክክርም በኮሪያ ልሳነ ምድር የሚስተዋለውን ውጥረት ይበልጥ እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡
በራስ አቅም የተሰራችው የስለላ ሳተላይት በስኬት ወደ ህዋ ደርሳ ተልዕኮዋን እየፈጸመች መሆኑንም የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የስለላ ሳተላይቷ መሬት ላይ እስከ 30 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያላቸው ነገሮችን የመለየት አቅም እንዳላት ነው የተገለጸው፡፡
ሴኡል ከዚህ በፊት የአሜሪካ የንግድ እና ወታደራዊ ሳተላይቶችን ለተለያዩ ዓላማዎች ስትጠቀም እንደነበር አርቲ ዘግቧል፡፡
ሀገሪቱ በራሷ አቅም ሳተላይት ማምጠቅ መጀመሯ በወታደራዊና ሌሎች ዘርፎች ያላትን አቅም ይበልጥ ማጠናከር እንደሚያስችላት ተገልጿል፡፡
ደቡብ ኮሪያ የአሁኗን ጨመሮ እስከ 2025 ድረስ አምስት የስለላ ሳተላይቶችን ወደ ህዋ ለማምጠቅ ማቀዷተመላክቷል፡፡