Fana: At a Speed of Life!

ለዘላቂ ሰላም የድርሻቸውን እንደሚወጡ የተሃድሶ ሰልጣኞች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተሃድሶ ስልጠና ያገኘነውን ዕውቀት ተጠቅመን ለአካባቢያችን ዘላቂ ሰላም የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ በኮምቦልቻ ጮሬሳ ጊዜያዊ ማቆያ የተሃድሶ ስልጠና ያጠናቀቁ ግለሰቦች ገለጹ።

በምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት የኮምቦልቻ ጮሪሳ ጊዜያዊ ማቆያ የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ ግልሰቦች ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለዋል።

ከሰልጣኞቹ መካከል አቶ ታደሰ ግዛው እንዳሉት÷ በጊዜያዊ ማቆያው በተሰጠው ስልጠና ስለ አማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ፣ ስለ ሰላም አስፈላጊነት፣ ስለ አብሮነትና የግጭት አስከፊነት በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በቆይታዬ ሰብዓዊ መብቴ ተጠብቋል፤ ከስህተታችን ተምረናል ለዘላቂ ሰላም መስፈን ራሳችንን አዘጋጅተናል ብለዋል።

አቶ የአብቃል ቢታው በበኩላቸው÷ ስለ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታና አብሮነት የተሰጣቸው ስልጠና አሁን ያጋጠመውን ችግር በትክክል ተገንዝበው ለዘላቂ ሰላም የድርሻቸውን ለመወጣት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በተፈጠረላቸው ግንዛቤም የተሳሳቱትን ወደ ሰላም እንዲመጡ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ከተሃድሶ ስልጠናው ያገኘሁትን ዕውቀት ተጠቅሜ ስለ ሰላምና አብሮነት አስተምራለሁ ያለችው ደግሞ ወይዘሪት ጤና ጌትነት ናት።

በፌዴራል ፖሊስ የሰሜን ምስራቅ ሬጅመንት አምስት ሻለቃ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ኩራባቸው እንዳለ በበኩላቸው÷ የተሳሳቱ ግለሰቦችን በማስተማር የመመለስ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሰልጣኞች በቆይታቸው የሀገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ አውቀው ለአካባቢያቸው ሰላም ዘብ እንዲቆሙ ግንዛቤ እንዲያገኙ ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

እርስ በርስ እያጋጩ ችግር የሚፈጥሩትን ሁላችንም መታገልና ማውገዝ ይኖርብናል ያሉት ደግሞ በፌዴራል ፖሊስ ሰሜን ምስራቅ መምሪያ ምክትል አዛዥ ኮማንደር ሰይድ እንድሪስ ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.