እስራዔል እና ሃማስ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ሥምምነቱን ሊያራዝሙ ነው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራዔል እና ሃማስ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ሥምምነቱን ሊያራዝሙ መዘጋጀታቸው ተሰማ፡፡
በማስማማቱ በኩል ሚናዋን ስትጫወት የነበረችው ኳታር ዛሬ የሚያበቃውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ሥምምነት ሁለቱ ወገኖች እንደሚያራዝሙት ጠቁማለች፡፡
የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማጅድ አል አንሳሪ ÷ የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ሥምምነቱ በጋዛ ሰርጥ ለተጨማሪ ሁለት ቀናት እንዲራዘም ሥምምነት ላይ ተደርሷል ማለታቸውም ተገልጿል።
ሃማስ በበኩሉ መረጃው እውነት ስለመሆኑ በሰጠው መግለጫ አረጋግጧል፡፡
ኳታር እና ግብፅ ከአሜሪካ ጋር በመተባበር የተኩስ አቁም ሥምምነቱ ለተጨማሪ ሁለት ቀናት እንዲራዘም እንዳስማሟቸውም ተጠቁሟል።
ታጋቾችን እና እስረኞችን የመለዋወጡ ሥራ እንደሚቀጥል መገለጹን ቢዝነስ ሪከርደር አስነብቧል፡፡
ሁለቱ ወገኖች “ሰብዓዊ የተኩስ አቁም” በሚል ሥምምነት እስከ ዛሬ ወዳቆሙት ጦርነት ዳግም እንዳይመለሱ ዓለም አቀፋዊ ጫና ሲደረግባቸው መቆየቱ ይታወሳል፡፡