Fana: At a Speed of Life!

“ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ” ጉባዔ ኢትዮጵያ ተሰሚነቷ እየጨመረ መምጣቱ የተረጋገጠበት መድረክ ነበር-አቶ ማሞ ምህረቱ

አዲስ አበባ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ” ጉባዔ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ተሰሚነቷ እየጨመረ መምጣቱ የተረጋገጠበት ውጤታማ ውይይት ነበር ሲሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ተናገሩ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የጀርመን ቆይታን በተመለከተ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ በሰጡት ማብራሪያ÷ በጀርመን የተካሄደው “ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ “ጉባዔ በዋንኛነት ኢኮኖሚ ላይ ትኩረቱን ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ጀርመን እንዲሁም አውሮፓ ከአፍሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር ይፈልጋሉ ያሉት አቶ ማሞ ይህንን ለማድረግ ውይይቱ ጥሩ መደላድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡

ከጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ጋር በተደረገው ውይይት በተለያዩ ዘርፎች ላይ አብሮ ለመስራት ከስምምነት መደረሱንም ተናግረዋል፡፡

በዚህ ረገድ ሰፊ ስራዎች ይሰራሉ ከተባሉት ውስጥ በታዳሽ ሃይል ፣ማዳበሪያ ላይ እና መንግስት እያደረገ ያለውን የኢኮኖሚ ሪፎርም መደገፍ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ከዚህ ውይይት ከተገኘው ውጤት ውስጥ ጀርመን በፈረንጆች አቆጣጠር 2030 ለ ኢዩ አፍሪካ ግሪን ኢነርጂ ኢኒሼቲቭ 4 ቢሊየን ዩሮ እንደምትመድብ ቃል መግባቷን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ትሆናለች ብለን እንጠብቃለን ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም ውይይቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጋር ያቀናው ልዑክ ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር ለመነጋገር እና ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ለመወያየት እድል የሰጠ ነው ብለዋል፡፡

በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ መንግስት አመለካከት ምን እንደሆነም ለማንፀባረቅ እድል የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ መንግስት እየሰራ ያለውን ስራ በነበረው ውይይት ለማስረዳት ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል ነው ያሉት አቶ ማሞ ምህረቱ ፡፡

ኢትዮጵያ ድምጿን ያሰማችበት ፣ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ተሰሚነቷ እየጨመረ መምጣቱ የተረጋገጠበት ውጤታማ ውይይት ነበር ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር መምከራቸውን አንስተው በውይይቱም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት መገምገማቸውን እና ሀገራዊ እና ቀጠናዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን አንስተዋል፡፡

ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የኢኮኖሚ ሪፎርም የፈረንሳይ መንግስት በሚደግፍበት መንገዶች ላይም መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.