ሕዝቡ ውስጣዊ አንድነቱን በመጠበቅ የጥፋት ቡድኖችን ሴራ ማክሸፍ እንዳለበት ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝቡ ውስጣዊ አንድነቱን በመጠበቅ የጥፋት ቡድኖችን ሴራ ፊት ለፊት ታግሎ ማሸነፍ እንዳለበት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለፁ።
በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከወረባቦ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በቢስቲማ ከተማ ዛሬ ውይይት ተካሂዷል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ በተሰራው ህግን የማስከበር ስራ የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መምጣት ችሏል።
ይሄንን ለማጠናከርም ህዝቡ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሰሩ ጽንፈኞችን መታገል እንዳለበት ገልፀዋል።
በተገኘው ሰላምም ሥራ አቋርጠው የነበሩ የህዝብና የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰው÷ ይህንኑ ዘላቂ ለማድረግም በጠንካራ ትብብር መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ መኮንን በበኩላቸው÷ በዞኑ አስተማማኝ ሰላም በማስፈን የጀመርናቸውን ልማቶች ለማስቀጠል ከህዝቡ ጋር በየደረጃው ውይይቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት ሰላም ፈላጊውን ህዝብ በማስተባበር በተሰራው ሥራ ውጤት መገኘቱን ገልጸው÷ በቀጣይም ለልማት እንቅፋት የማይሆን አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
በምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት የደቡብ ወሎና የደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጀነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ÷ የመከላከያ ሰራዊት ሰላምን በማስከበር ጠንካራ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።
ህዝቡ ከሰራዊቱ ጎን ተሰልፎ እየሰራ ያለው ሰላምን የማስከበር እንቅስቃሴ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበትም ተናግረዋል።
ህዝቡን በብሄርና በእምነት ከፋፍለው የግል ጥቅማቸውን ማካበት የሚፈልጉ ጽንፈኞች የመከላከያ ሠራዊትን ስም እያጠፉ መሆኑን ጠቁመው ነገር ግን ሰራዊቱ ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን ህብረተሰቡን በተለያየ የልማት ስራ በማገዝ ህዝባዊነቱን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም መንግስትና ህዝብን እያቃቃሩ ሰላም የሚነሱና ህግ እንዳይከበር የሚያደርጉ ሴረኞችን በጋራ መታገልና ስርዓት ማስያዝ ከሁሉም ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም÷ ስራ አጥነት እንዲቀረፍ፣ ሰርተን አንድንበላና ወጥተን መግባት እንድንችል ሰላም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሰላም ማስከበር የጋራ ጥረትንና ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው÷ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፈው ሰላም የማስከበር ስራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊትን ስም በማጥፋት ግጭት የሚቀሰቅሱ ኃይሎችን ሐሳብ ሳንቀበል ለሰላማችን እንሰራለን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ቀደም ሲል በነበረው ጦርነት የተጎዳነው እኛው በመሆናችን ጦርነት አንፈልግም፤ ለሰላም እንሰራለን ሱሉም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም ተሳታፊ ሆነዋል።