ብሔራዊ የምክክር ሂደቱ ሊባክን የማይገባው ዕድል መሆኑ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉትሥድስት አሥርት ዓመታት ሞክራው ያልተሳካላት ብሔራዊ ምክክር ሊባክን የማይገባው ወርቃማ ዕድል መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናት እና ምርምር ተቋም ምሁር ደሣለኝ አምሳሉ (ተ/ፕ) ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ “ብሔራዊ የምክክር ሂደቱ ሊባክን የማይገባው መልካም ዕድል” መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
ችግሮቻችን ዘመናትን አብረውን ሊሻገሩ አይገባም ያሉት ምሁሩ÷ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ከችግሮች ለመውጣት የሚያስችል አንድ ዕድል ይዞ መጥቷል ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያውያን የሚበጅ ፣ ተዓማኒ እና ሚዛናዊ ሥራ እንዲያከናውንም ዜጎች የሠጥቶ – መቀበል መርኅን ከግምት ውስጥ በማስገባት በምክክሩ ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው መክረዋል፡፡
በኮሚሽኑ አማካኝነት ሕዝብን ለማሳተፍ በሚዘጋጁ መድረኮች እና በሚዘረጉ ሥርዓቶች ሁሉ ሕዝቡ በትጋት በመሳተፍ ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማበጀት የተገኙ ወርቃማ ዕድሎችን ችላ ማለት እንደማይገባው ነው ያስገነዘቡት፡፡
በመራዖል ከድር