Fana: At a Speed of Life!

ኬንያ በዓመት 20 ሺህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ለማስገባት ማቀዷ ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኬንያ በነዳጅ ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ በየዓመቱ 20 ሺህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ ለማስገባት ማቀዷ ተገለጸ፡፡

ኬንያ ዕቅዱን ያወጣችው በሀገሪቷ እያደገ የመጣውን የተሽከርካሪ ግዢ ፍላጎት ለማሟላትና የነዳጅ ፍጆታዋን በዘላቂነት ለመቀነስ ነው ተብሏል፡፡

በፈረንጆቹ 2023 ላይ የወጣው የኬንያ የምጣኔ-ሐብት ሪፖርት እንደሚያመላክተው ኬንያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ትኩረት ሠጥታ ከውጭ ለማስገባት ያቀደችው በነዳጅ ላይ ጥገኛ በመሆኗ በሀገሪቷ ላይ የኑሮ ውድነት ጫና መፍጠሩን ተከትሎ እንደሆነ ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡

የኬንያ የፖሊሲ ጥናትና ትንተና ተቋም መረጃ እንደሚያሳየው ÷ ሀገሪቷ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስገባት እንደ ሀገር የነዳጅ ወጪዋን መቀነስ ብቻ ሳይሆን ሕዝቦቿም ለመጓጓዣ የሚያወጡት ገንዘብ ሒሳብም በእጅጉ እንደሚቀንስላቸው ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኑሮ ውድነትም ይቀንሳል ተብሏል፡፡

የኬንያ መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር በወሰደው እርምጃ ከወር በፊት የነበረውን 7 ነጥብ 3 በመቶ የዋጋ ግሽበት ወደ 6 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን የሀገሪቷ ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡

የዋጋ ግሽበቱን በምግብ ሸቀጦች ላይ ማስተካከል ሲቻል የነዳጅን ዋጋ ግን መቆጣጠር እንዳልተቻለ ነው የተገለጸው፡፡

በሌላም በኩል የኤሌክትሪክ መጓጓዣ አገልግሎትን ዕውን ማድረግ ዓለም ከተበከለ ዓየር ነጻ ለመሆን የምትከተለውን የአማራጭ ኃይል ሥርዓት ፖሊሲ ሽግግር ያፋጥነዋል ተብሏል።

ኬንያ አሁን ላይ ይህን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ መፈለጓ አዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመቀበልና በራሷ አምርታ ወደ ሌሎች ሀገራት ለመላክ ውድድሩ ቀላል ይሆንላታልም ነው የተባለው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.