አቶ አሕመድ ሽዴ ሳዑዲ በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ላይ እገዛ እንደምታደርግ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ለማገዝ ዝግጁ እንደሆነች የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
አቶ አሕመድ ሽዴ በሳዑዲ አፍሪካ ጉባዔ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ የነበረውን ቆይታን በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ፤ ልዑኩ ከተለያዩ የሳውዲ የልማት የፋይናንስ ተቋማት ጋር ውይይት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
የሳዑዲ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮንፍረንስ ላይም ልዑኩ ተሳትፎ ማድረጉን ጠቅሰው÷ የሳዑዲና የኢትዮጵያ መንግስት የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የሀገራቱ ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ትስስር፣ የመልክዓ ምድራዊ ቁርኝትና ቅርበት እንዲሁም የሀይማኖትና የባህልም ትስስር ያላቸው መሆናቸውን አብራርተዋል።
በተለይም የሳዑዲ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ሀገሪቱ በልማት ፋይናንስ አቅርቦት ኢትዮጵያን ከሚደግፉ ሀገሮች አንዷ ነች ብለዋል።
በሰላምና በቀጣናዊ ትስስርም በጋራ እየተሰራ እንደሆነ አንስተው፤ በተጨማሪም የኢትዮ ሳዑዲ ግንኙነት ጠንካራ ወዳጅነትና አጋርነት ያለበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግንኙነቱ እያደገ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው ልኡክ አካል የሆነው ቡድን ከሳዑዲ መንግስት ጋር በነዳጅና በኢነርጂ ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግስት ለመንግስት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል ብለዋል፡፡
የመግባቢያ ሰነዱ ዋና አላማም የነዳጅ አቅርቦትን ከኢትዮጵያ ጋር ለማድረግ ያለመ ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ በቴክኖሎጂ፣ በነዳጅና በሀይል አጠቃቀም ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ያላቸውን ግንኙት ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ከሳዑዲ የገንዘብ ሚኒስትር ጋር ውይይት መካሄዱንና የሳዑዲ መንግስት በተለይ በልማት ፋይናንስ ኢትዮጵያን ሲያግዝ እንደቆየ ገልጸው÷ በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ላይም እገዛ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል ብለዋል፡፡