ከ60 ዓመታት በፊት ዝርያው እንደጠፋ የተነገረለት ጃርት መሰል እንስሳ መታየቱ ተነገረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ60 ዓመት በፊት ዝርያው ጠፍቷል የተባለው ‘ኢችድና’ የተሰኘ ጃርት መሰል እንስሳ በድጋሚ መታየቱን ሳይንቲስቶች አስታወቁ፡፡
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባዮሎጂስት በሆነው ዴቪድ አንቲቦሮ የተገኘው ይህ አጥቢ እንስሳ ለስድስት አስርት ዓመታት ጠፍቶ እንደደነበር የተገለፀ ሲሆን በድጋሚ በኢንዶኔዥያ ተራሮች ላይ መገኘቱ ተገልጿል፡፡
ኢችድናዎች ዝርያቸው በመላ አውስትራሊያና በኒው ጊኒ ቆላማ ስፍራዎች እንደሚገኝ በፈረንጆቹ 1961 ተመዝግቦ ነበር።
ይህ ከሆነ በኋላ ሳይታዩ የቆዩት ኢችድናዎች በቅርቡ በኢንዶኔዥያ ብቅ ማለታቸው ተነግሯል።
ከኢችድና በተጨማሪ በኢንዶኔዥያ ተራሮች አዳዲስ የነፍሳት እና የእንቁራሪት ዝርያዎችን፣ ካንጋሮ እና የገነት ወፎች (ፓራዳይዝ በርድስ) የተባሉትን የወፍ ዝርያዎች እንደታዩ የሳይንቲስቶች ቡድኑ አስታውቋል።
ኢችድናዎች (ጃርት መሰል እንስሳዎች) ሾጣጣ ፊት፣ ፀጉራማ እና ሹል ምንቃር ያላቸው ሲሆን ከ200 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ዳይኖሰሮች ይኖሩ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ይኖሩ እንደነበር ይገመታል፡፡
ኢቺድናዎች እንቁላል ጣይ ሆነው አጥቢ በመሆን ብቸኛ እንስሳ መሆናቸውም ተገልጿል።
በአለማችን ላይ አራት አይነት የኢችድና ዝርያዎች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን ምዕራባዊ ኢችድና በሚል የሚጠራው ዝርያ በከፍተኛ ደረጃ የመጥፋት አደጋ እንደገጠመው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡