ለሥራ ፈጠራ ሀሳብ ውድድር ምቹ ሥነ-ምህዳር ለመፍጠር ቅንጅታዊ ስራ ይጠይቃል- አቶ ንጉሱ ጥላሁን
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሥራ ፈጠራ ሀሳብ ውድድር ምቹ ሥነ-ምህዳር ለመፍጠር የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ፡፡
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተዘጋጀ ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ምቹ ስነ-ምህዳር መፍጠርና የብሩህ ኢትዮጵያ 2016 የፈጠራ ሀሳብ ውድድር ላይ ያተኮረ የባለድርሻና አጋር አካላት የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
አቶ ንጉሡ ጥላሁን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ ሚኒስቴሩ ለጀማሪ ሥራ ዕድል ፈጣሪዎችና ኢንተርፕራይዞች ምስረታ ምቹ የሆነ ስነ-ምህዳር ለመፍጠር ሰፋፊ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡
በዚህም የብሩህ ኢትዮጵን ጨምሮ የተለያዩ ውድድሮችን በየደረጃው ከማካሄድ ባለፈ የማሰልጠን፣ የመሸለምና ተከታትሎ የማብቃት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
ለሥራ ፈጠራ ሀሳብ ውድድር ምቹ የሆነ ስነ-ምህዳር ለመፍጠር አስፈፃሚ፣ ባለድርሻ እና አጋር አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል ፡፡
በግሉ ዘርፍ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችንና ስታርታፖችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጀምር ሥራዎች መኖራቸውን ያመሱት አቶ ንጉሡ÷ የከፍተኛ ትምህርት፣ የጥናትና ምርምርና የፋይናንስ ተቋማት በሂደቱ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡