Fana: At a Speed of Life!

የጤና ፋይናንስን በማሻሻል ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋንን ለማሳካት እየተሰራ ነው – ዶ/ር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ፋይናንስን በማሻሻል ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋንን ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።

‘ጠንካራ የጤና ፋይናንስ ለዘላቂ የጤና ልማት’ በሚል መሪ ሀሳብ 25ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ዶ/ር ሊያግጭቶች፣ ድርቅ፣ የተለያዩ ወረርሽኞች እና መሰል ክስቶች የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመው፤ በተለይም የወባ በሽታከ2014 ዓ.ም ወዲህ እየጨመረ መምጣቱ የዘርፉ ፈተና መሆኑን ተናግረዋል።

በ2014 ዓ.ም 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎች፣ በ2015 ዓ.ም ደግሞ 3 ነጥብ 3 ማሊየን ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን አስታውሰው፤ ይህም በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ማሻቀቡን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ወባን ጨምሮ የኮሌራ እና መሰል ወረርሽኞችን መከላከልና መቆጣጠር በተጀመረው የቀጣይ 3 ዓመት እቅድ ላይ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የሀገር ውስጥ መድሀኒት አምራቾችን በማሳደግ በመድሀኒት አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች የወደሙ የጤና ተቋማትን ወደ ስራ ማስገባትም የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አንስተዋል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው÷ አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማእከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመዲናዋ ባሉ ጤና ተቋማት ለሁሉም ተደራሽ ተመጣጣኝ እና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንዲቻል በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አንስተዋል።

በዙፋን ካሳሁን እና ሳሙኤል ወርቃየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.