የኢትዮጵያ ታምርት ስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ ተካሄደ።
በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እና የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
የስትሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢ ደመቀ መኮንን በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የምጣኔ ሃብት ዕድገት መሰረት በመሆኑ በልዩ ትኩረት ትብብር ሊሰራበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ንቅናቄው የዘርፉን ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታትና ትልቅ ውጤት ለማስመዝገብ ማስቻሉን ጠቅሰው፤ ለንቅናቄው ስኬት ቁልፍ ሚና ያለው ስትሪንግ ኮሚቴው ለችግሮች ፈጣን ምላሽ በመስጠት በቁርጠኝነት እንዲሰራ አስገንዝበዋል።
ከፖሊሲና አሰራር ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅንጅት መፍታት ለነገ የማይባል ተግባር ሆኖ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።
በመድረኩ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተሰሩ ስራዎች አፈፃፀም እና ቀጣይ እቅዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በዚህም ንቅናቄው በ2015 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ከተከፈተ በኋላ በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች በተቋቋመው ስትሪንግ ኮሚቴ የተለያዩ ስራዎችን መከናወናቸው ተመላክቷል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተሰሩ ስራዎች በተለያየ ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መግባታቸው ይታወቃል።
በትዝታ ደሳለኝ